ምዕራፍ 103
1ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኪ፥ አጥንቶቼም ሁሉ፥ የተቀደሰ ስሙን።
2ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኪ፥ ምስጋናውንም ሁሉ አትርሺ፤
3ኃጢአትሽን ሁሉ ይቅር የሚል፥ ደዌሽንም ሁሉ የሚፈውስ፥
4ሕይወትሽን ከጥፋት የሚያድናት፥ በምሕረቱና በቸርነቱ የሚከልልሽ፥
5ምኞትሽን ከበረከቱ የሚያጠግባት፥ ጕልማስነትሽን እንደ ንስር ያድሳል።
6እግዚአብሔር ይቅርታ አድራጊ ነው፤ ለተበደሉ ሁሉ ይፈርዳል።
7ለሙሴ መንገዱን አስታወቀ፥ ለእስራኤል ልጆችም አደራረጉን።
8እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ ነው፥ ከቍጣ የራቀ ምሕረቱም የበዛ።
9ሁልጊዜም አይቀሥፍም፥ ለዘላለምም አይቈጣም።
10እንደ ኃጢአታችን አላደረገብንም፥ እንደ በደላችንም አልከፈለንም።
11ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፥ እንዲሁ እግዚአብሔር ምሕረቱን በሚፈሩት ላይ አጠነከረ።
12ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፥ እንዲሁ ኃጢአታችንን ከእኛ አራቀ።
13አባት ለልጆቹ እንደሚራራ እንዲሁ እግዚአብሔር ለሚፈሩት ይራራል፤
14ፍጥረታችንን እርሱ ያውቃልና፤ አቤቱ፥ እኛ አፈር እንደ ሆንን አስብ።
15ሰውስ ዘመኑ እንደ ሣር ነው፤ እንደ ዱር አበባ እንዲሁ ያብባል፤
16ነፋስ በነፈሰበት ጊዜ ያልፋልና፥ ስፍራውንም ደግሞ አያውቀውምና።
17የእግዚአብሔር ምሕረት ግን ከዘላለም እስከ ዘላለም በሚፈሩት ላይ፥ ጽድቁም በልጅ ልጆች ላይ ነው፤
18ቃል ኪዳኑን በሚጠብቁ፥ ትእዛዙንም ያደርጉአት ዘንድ በሚያስቡ ላይ ነው።
19እግዚአብሔር ዙፋኑን በሰማይ አዘጋጀ፥ መንግሥቱም ሁሉን ትገዛለች።
20ቃሉን የምትፈጽሙ፥ ብርቱዎችና ኃያላን፥ የቃሉንም ድምፅ የምትሰሙ መላእክቱ ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ባርኩ።
21ሠራዊቱ ሁሉ፥ ፈቃዱን የምታደርጉ አገልጋዮቹ፥ እግዚአብሔርን ባርኩ።
22ፍጥረቶቹ ሁሉ በግዛቱ ስፍራ ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ባርኩ። ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኪ።