ምዕራፍ 106
1ሃሌ ሉያ፤ ቸር ነውና፥ ምህረቱም ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ።
2የእግዚአብሔርን ኃይል ሥራ ማን ይናገራል? ምስጋናውንስ ሁሉ ማን ያሰማል?
3ፍርድን የሚጠብቁ፥ ጽድቅንም ሁልጊዜ የሚያደርጉ ምስጉኖች ናቸው።
4አቤቱ፥ በሕዝብህ ሞገስ አስበን፥ በመድኃኒትህም ጐብኘን፤
5የመረጥሃቸውን በጎነት እናይ ዘንድ፥ በሕዝብህም ደስታ ደስ ይለን ዘንድ፥ ከርስትህም ጋር እንጓደድ ዘንድ።
6ከአባቶቻችን ጋር ኃጢአትን ሠራን፥ ዐመፅንም፥ በደልንም።
7አባቶቻችን በግብጽ ሳሉ ተኣምራትህን አላስተዋሉም፥ የምሕረትህንም ብዛት አላሰቡም፤ በኤርትራ ባሕር ባለፉ ጊዜ ዐመፁብህ።
8ኃይሉን ግን ለማስታወቅ። ስለ ስሙ አዳናቸው።
9የኤርትራንም ባሕር ገሠጸ እርሱም ደረቀ፤ እንደ ምድረ በዳ በጥልቅ መራቸው።
10ከሚጠሉአቸውም እጅ አዳናቸው፥ ከጠላትም እጅ ተቤዣቸው።
11ያሳደዱአቸውንም ውኃ ደፈናቸው፥ ከእነርሱም አንድ አልቀረም።
12በዚያን ጊዜ በቃሉ አመኑ፥ ምስጋናውንም ዘመሩ።
13ፈጥነውም ሥራውን ረሱ፥ በምክሩም አልታገሡም።
14በምድረ በዳም ምኞትን ተመኙ፥ በበረሃም እግዚአብሔርን ተፈታተኑት።
15የለመኑትንም ሰጣቸው፤ ለነፍሳቸው ግን ክሳትን ላከ።
16ሙሴንም እግዚአብሔር የቀደሰውንም አሮንን በሰፈር ተመቀኙአቸው።
17ምድርም ተከፈተች ዳታንንም ዋጠችው፥ የአቤሮንንም ወገን ደፈነች፤
18በማኅበራቸውም እሳት ነደደች፥ ነበልባልም ኅጥኣንን አቃጠላቸው።
19በኮሬብም ጥጃን ሠሩ፥ ቀልጦ ለተሠራ ምስልም ሰገዱ።
20ሣርም በሚበላ በበሬ ምሳሌ ክብራቸውን ለወጡ።
21-
22ታላቅ ነገርንም በግብጽ፥ ድንቅንም በካራን ምድር፥ ግሩም ነገርንም በኤርትራ ባሕር ያደረገውን ያዳናቸውንም እግዚአብሔርን ረሱ።
23እንዳያጠፋቸው ቍጣውን ይመልስ ዘንድ የተመረጠው ሙሴ በመቅሠፍት ጊዜ በፊቱ ባይቆም ኖሮ፥ ያጠፋቸው ዘንድ ተናገረ።
24የተወደደችውን ምድር ናቁ፥ በቃሉም አልታመኑም፥
25በድንኳኖቻቸውም ውስጥ አንጐራጐሩ፤ የእግዚአብሔርን ቃል አልሰሙም።
26-
27በምድረ በዳም ይጥላቸው ዘንድ፥ ዘራቸውንም በአሕዛብ መካከል ይጥል ዘንድ፥ በየአገሩም ይበትናቸው ዘንድ፥ እጁን አነሣባቸው።
28በብዔል ፌጎርም ተባበሩበት፥ የሙታንንም መሥዋዕት በሉ።
29በሥራቸውም አስመረሩት፥ ቸነፈርም በላያቸው በዛ።
30ፊንሐስም ተነሥቶ ፈረደባቸው፥ ቸነፈሩም ተወ፤
31ያም እስከ ዘላለም ለልጅ ልጅ ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት።
32-
33በክርክር ውኃ ዘንድም አስቈጡት፥ መንፈሱን አስመርረዋታልና፤ ስለ እነርሱም ሙሴ ተበሳጨ፤ በከንፈሮቹም በስንፍና ተናገረ።
34እግዚአብሔርም እንዳላቸው አሕዛብን አላጠፉም፤
35ከአሕዛብም ጋር ተደባለቁ፥ ሥራቸውንም ተማሩ።
36ለጣዖቶቻቸውም ተገዙ፥ ወጥመድም ሆኑባቸው።
37ወንዶች ልጆቻቸውንና ሴቶች ልጆቻቸውን ለአጋንንት ሠው፤
38የወንዶች ልጆቻቸውንና የሴቶች ልጆቻቸን ደም፥ ለከነዓን ጣዖቶች የሠውአቸውን ንጹሕ ደም አፈሰሱ፥ ምድርም በደም ረከሰች።
39በሥራቸው ረከሱ፥ በማድረጋቸውም አመነዘሩ።
40የእግዚአብሔርም ቍጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ፥ ርስቱንም ተጸየፈ።
41ወደ አሕዛብም እጅ አሳለፋቸው፥ የሚጠሉአቸውም ገዙአቸው።
42ጠላቶቻቸውም ግፍ አደረጉባቸው፥ ከእጃቸውም በታች ተዋረዱ።
43ብዙ ጊዜ አዳናቸው፤ ነገር ግን በምክራቸው አስመረሩት፥ በኃጢአታቸውም ተዋረዱ።
44እርሱ ግን ጩኸታቸውን በሰማ ጊዜ ጭንቃቸውን ተመለከተ፤
45ለእነርሱም ኪዳኑን አሰበ፥ እንደ ምሕረቱም ብዛት ተጸጸተ።
46በማረኩአቸውም ሁሉ ፊት ሞገስን ሰጣቸው።
47አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ፥ አድነን፤ ቅዱስ ስምህን እናመሰግን ዘንድ፥ በምስጋናህም እንመካ ዘንድ፥ ከአሕዛብ መካከል ሰብስበን።
48ከዘላለም እስከ ዘላለም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ ሕዝብም ሁሉ አሜን ይበል። ሃሌ ሉያ።