ምዕራፍ 108
1ልቤ ጽኑ ነው፥ አቤቱ፥ ልቤ ጽኑ ነው፤ እቀኛለሁ በክብሬም እዘምራለሁ።
2በገና ሆይ፥ ተነሥ፥ መሰንቆም፤ እኔም ማልጄ እነሣለሁ።
3አቤቱ፥ በአሕዛብ መካከል አመሰግንሃለሁ፥ በወገኖችም መካከል እዘምርልሃለሁ፤
4ምሕረትህ በሰማይ ላይ ታላቅ ናትና፥ እውነትህም እስከ ደመናት ድረስ ነውና።
5አቤቱ፥ በሰማያት ላይ ከፍ ከፍ በል፥ ክብርህም በምድር ሁሉ ላይ ትሁን።
6ወዳጆችህ ይድኑ ዘንድ፤ በቀኝህ አድን አድምጠኝም።
7እግዚአብሔር በቅድስናው ተናገረ። ደስ ይለኛል፥ ሴኬምንም እካፈላለሁ፥ የሱኮትንም ሸለቆ እሰፍራለሁ።
8ገለዓድ የእኔ ነው ምናሴም የእኔ ነው፤ ኤፍሬም የራሴ መጠጊያ ነው። ይሁዳ ንጉሤ ነው።
9ሞዓብ መታጠቢያዬ ነው፥ በኤዶምያስ ላይም ጫማዬን እዘረጋለሁ፤ ፍልስጥኤም ይገዙልኛል።
10ወደ ጽኑ ከተማ ማን ይወስደኛል? ማንስ እስከ ኤዶምያስ ይመራኛል?
11አቤቱ፥ የጣልኸኝ አንተ አይደለህምን? አምላክ ሆይ፥ ከሠራዊታችን ጋር አትወጣም።
12በመከራችን ረድኤትን ስጠን፤ የሰውም ማዳን ከንቱ ነው።
13በእግዚአብሔር ኃይልን እናደርጋለን፤ እርሱም የሚያስጨንቁንን ያዋርዳቸዋል።