English

ምዕራፍ 112

1ሃሌ ሉያ። እግዚአብሔርን የሚፈራ፥ ትእዛዙንም እጅግ የሚወድድ ሰው ምስጉን ነው።
2ዘሩ በምድር ላይ ኃያል ይሆናል፤ የቅኖች ትውልድ ትባረካለች።
3ክብርና ባለጠግነት በቤቱ ነው፥ ጽድቁም ለዘላለም ይኖራል።
4ለቅኖች ብርሃን በጨለማ ወጣ፤ መሓሪና ይቅር ባይ ጻድቅም ነው።
5ቸር ሰው ይራራል ያበድራልም፥ በፍርድም ነገሩን ይፈጽማል።
6ለዘላለም አይናወጥም፤ የጻድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል።
7ከክፉ ነገር አይፈራም፤ በእግዚአብሔር ለመታመን ልቡ የጸና ነው።
8በጠላቶቹ ላይ እስኪያይ ድረስ ልቡ ጽኑ ነው፥ አይፈራም።
9በተነ ለችግረኞችም ሰጠ፤ ጽድቁ ለዘላለም ዓለም ይኖራል፤ ቀንዱ በክብር ከፍ ከፍ ይላል።
10ኃጢአተኛም አይቶ ይቈጣል፥ ጥርሱንም ያፋጫል፥ ይቀልጣልም፤ የኃጢአተኞችም ምኞት ትጠፋለች።