ምዕራፍ 13
1አቤቱ፥ እስከ መቼ ፈጽመህ ትረሳኛለህ? እስከ መቼስ ፊትህን ከእኔ ትሰውራለህ?
2እስከ መቼ በነፍሴ እመካከራለሁ? ትካዜስ እስከ መቼ ሁልጊዜ ይሆናል? እስከ መቼ ጠላቴ በላዬ ይጓደዳል?
3አቤቱ አምላኬ፥ እየኝ ስማኝም፤ ጠላቴ። አሸነፍሁት እንዳይል፥
4የሚያስጨንቁኝም እኔ ብናወጥ ደስ እንዳይላቸው፥ ለሞትም እንዳልተኛ ዓይኖቼን አብራ።
5እኔ ግን በቸርነትህ ታመንሁ፥ ልቤም በመድኃኒትህ ደስ ይለዋል።
6የረዳኝን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፥ ለልዑል እግዚአብሔር ስምም እዘምራለሁ።