ምዕራፍ 148
1ሃሌ ሉያ። እግዚአብሔርን ከሰማያት አመስግኑት፤ በአርያም አመስግኑት።
2መላእክቱ ሁሉ፥ አመስግኑት፤ ሠራዊቱ ሁሉ፥ አመስግኑት።
3ፀሐይና ጨረቃ፥ አመስግኑት፤ ከዋክብትና ብርሃን ሁሉ፥ አመስግኑት።
4ሰማየ ሰማያት፥ አመስግኑት የሰማያት በላይም ውኃ።
5እርሱ ብሎአልና፥ ሆኑም፤ እርሱም አዝዞአልና፥ ተፈጠሩም፤ የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑት።
6ለዘላለም ዓለም አቆማቸው፤ ትእዛዝን ሰጠ፥ አያልፉምም።
7እባቦች ጥልቆችም ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ከምድር አመስግኑት፤
8እሳትና በረዶ አመዳይና ውርጭ፥ ቃሉን የሚያደርግ ዐውሎ ነፋስም፤
9ተራሮች ኰረብቶችም ሁሉ፥ የሚያፈራም ዛፍ ዝግባም ሁሉ፤
10አራዊትም እንስሳትም ሁሉ፥ ተንቀሳቃሾችም የሚበርሩ ወፎችም፤
11የምድር ነገሥታት አሕዛብም ሁሉ፥ አለቆች የምድርም ፈራጆች ሁሉ፥
12ጕልማሶችና ቈነጃጅቶች፥ ሽማግሌዎችና ልጆች፤
13የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑ፤ ስሙ ብቻውን ከፍ ከፍ ብሎአልና፥ ምስጋናውም በሰማይና በምድር ላይ ነው።
14የሕዝቡንም ቀንድ ከፍ ከፍ ያደርጋል፤ የቅዱሳኑንም ሁሉ ምስጋና ወደ እርሱ ለቀረበ ለእስራኤል ልጆች ሕዝብ ከፍ ከፍ ያደርጋል። ሃሌ ሉያ።