ምዕራፍ 18
1አቤቱ ጕልበቴ ሆይ፥ እወድድሃለሁ።
2እግዚአብሔር ዓለቴ፥ አምባዬ፥ መድኃኒቴ፥ አምላኬ፥ በእርሱም የምተማመንበት ረዳቴ፥ መታመኛዬና የደኅንነቴ ቀንድ መጠጊያዬም ነው።
3ምስጋና የሚገባውን እግዚአብሔርን እጠራለሁ፥ ከጠላቶቼም እድናለሁ።
4የሞት ጣር ያዘኝ፥ የዓመፅ ፈሳሽም አስፈራኝ፤
5የሲኦል ጣር ከበበኝ፤ የሞት ወጥመድም ደረሰብኝ።
6በጨነቀኝ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፥ ወደ አምላኬም ጮኽሁ፤ ከመቅደሱም ቃሌን ሰማኝ፥ ጩኸቴም በፊቱ ወደ ጆሮው ገባ።
7ምድርም ተንቀጠቀጠች ተናወጠችም፥ የተራሮችም መሠረቶች ተነቃነቁ፥ እግዚአብሔርም ተቈጥቶአልና ተንቀጠቀጡ።
8ከቍጣው ጢስ ወጣ፥ ከፊቱም የሚበላ እሳት ነደደ፤ ፍምም ከእርሱ በራ።
9ሰማዮችን ዝቅ ዝቅ አደረገ ወረደም፥ ጨለማ ከእግሩ በታች ነበረ።
10በኪሩቤልም ላይ ተቀምጦ በረረ፥ በነፋስም ክንፍ በረረ።
11መሰወሪያውን ጨለማ አደረገ፤ በዙሪያውም ድንኳኑ፤ በደመናት ውስጥ የጨለማ ውኃ ነበረ።
12በፊቱ ካለው ብርሃን የተነሣ ደመናትና በረዶ የእሳት ፍምም አለፉ።
13እግዚአብሔርም ከሰማያት አንጐደጐደ፥ ልዑልም ቃሉን ሰጠ።
14ፍላጻውን ላከ በተናቸውም፤ መብረቆችን አበዛ አወካቸውም።
15አቤቱ፥ ከዘለፋህ ከመዓትህም መንፈስ እስትንፋስ የተነሣ፥ የውኆች ምንጮች ታዩ፥ የዓለም መሠረቶችም ተገለጡ።
16ከላይ ሰደደ ወሰደኝም፥ ከብዙ ውኆችም አወጣኝ።
17ከብርቱዎች ጠላቶቼ ከሚጠሉኝም አዳነኝ፥ በርትተውብኝ ነበርና።
18በመከራዬ ቀን ደረሱብኝ፤ እግዚአብሔር ግን ደገፋዬ ሆነ።
19ወደ ሰፊ ስፍራም አወጣኝ፤ ወድዶኛልና አዳነኝ።
20እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ ይከፍለኛል፤ እንደ እጄ ንጽሕና ይመልስልኛል።
21የእግዚአብሔርን መንገድ ጠብቄአለሁና፥ በአምላኬም አላመፅሁም።
22ፍርዱ ሁሉ በፊቴ ነበረና፥ ሥርዓቱንም ከፊቴ አላራቅሁም።
23በእርሱ ዘንድ ቅን ነበርሁ፥ ከኃጢአቴም ተጠበቅሁ።
24እግዚአብሔርም እንደ ጽድቄ እንደ እጄም ንጽሕና በዓይኖቹ ፊት መለሰልኝ።
25ከቸር ሰው ጋር ቸር ሆነህ ትገኛለህ፤ ከቅን ሰው ጋር ቅን ሆነህ ትገኛለህ፤
26ከንጹሕ ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ፤ ከጠማማም ጋር ጠማማ ሆነህ ትገኛለህ።
27አንተ የተጠቃውን ሕዝብ ታድናለህና፥ የትዕቢተኞችን ዓይን ግን ታዋርዳለህ።
28አንተ መብራቴን ታበራለህና፤ እግዚአብሔር አምላኬ ጨለማዬን ያበራል።
29በአንተ ከጥፋት እድናለሁና በአምላኬም ቅጥሩን እዘልላለሁ።
30የአምላኬ መንገድ ፍጹም ነው፥ የእግዚአብሔር ቃል የነጠረ ነው፥ በእርሱ ለሚታመኑት ሁሉ ጋሻ ነው።
31ከእግዚአብሔር በቀር አምላክ ማን ነው? ከአምላካችን በቀር አምላክ ማን ነው?
32ኃይልን የሚያስታጥቀኝ መንገዴንም የሚያቃና፥
33እግሮቼን እንደ ብሖር እግሮች የሚያረታ በኮረብቶችም የሚያቆመኝ እግዚአብሔር ነው።
34እጆቼን ሰልፍ ያስተምራል፥ በክንዴም የናስ ቀስት እገትራለሁ።
35ለደኅንነቴም መታመኛን ሰጠኸኝ፥ ቀኝህም ትረዳኛለች፥ ትምህርትህም ለዘላለም ታጠናኛለች፥ ተግሣጽህም ታስተምረኛለች።
36አረማመዴን በበታቼ አሰፋህ፥ እግሮቼም አልተንሸራተቱም።
37ጠላቶቼን አሳድዳቸዋለሁ እይዛቸዋለሁም፥ እስካጠፋቸውም ድረስ አልመለስም።
38አስጨንቃቸዋለሁ መቆምም አይችሉም፥ ከእግሬም በታች ይወድቃሉ።
39ለሰልፍም ኃይልን ታስታጥቀኛለህ፤ በበላዬ የቆሙትን ሁሉ በበታቼ ታስገዛቸዋለህ።
40የጠላቶቼን ጀርባ ሰጠኸኝ፥ የሚጠሉኝንም አጠፋሃቸው።
41ጮኹ የሚረዳቸውም አልነበረም፤ ወደ እግዚአብሔርም ጮኹ አልሰማቸውም።
42እንደ ትቢያ በነፋስ ፊት እፈጫቸዋለሁ፥ እንደ አደባባይም ጭቃ እረግጣቸዋለሁ።
43ከሕዝብ ክርክር ታድነኛለህ፥ የአሕዛብም ራስ አድርገህ ትሾመኛለህ፥ የማላውቀው ሕዝብም ይገዛልኛል።
44በጆሮ ሰምተው ተገዙልኝ፤ የባዕድ ልጆች ደለሉኝ።
45የባዕድ ልጆች አረጁ፥ በመንገዳቸውም ተሰናከሉ።
46እግዚአብሔር ሕያው ነው፥ አምላኬም ቡሩክ ነው፥ የመድኃኒቴም አምላክ ከፍ ከፍ ይበል።
47በቀሌን የሚመልስልኝ አምላክ አሕዛብን በበታቼ ያስገዛልኛል።
48ከጠላቶቼ የሚታደገኝ እርሱ ነው፤ በእኔም ላይ ከቆሙ ከፍ ከፍ ታደርገኛለህ፥ ከግፈኛ ሰው ታድነኛለህ።
49አቤቱ፥ ስለዚህ በአሕዛብ ዘንድ አመሰግንሃለሁ፥ ለስምህም እዘምራለሁ።
50የንጉሡን መድኃኒት ታላቅ ያደርጋል፥ ቸርነቱንም ለቀባው ለዳዊትና ለዘሩ ለዘላለም ይሰጣል።