ምዕራፍ 2
1አሕዛብ ለምን ያጕረመርማሉ? ወገኖችስ ለምን ከንቱን ይናገራሉ?
2የምድር ነገሥታት ተነሡ፥ አለቆችም በእግዚአብሔርና በመሢሑ ላይ እንዲህ ሲሉ ተማከሩ።
3ማሰርያቸውን እንበጥስ፥ ገመዳቸውንም ከእኛ እንጣል።
4በሰማይ የሚኖር እርሱ ይሥቃል፥ ጌታም ይሣለቅባቸዋል።
5በዚያን ጊዜ በቍጣው ይናገራቸዋል፥ በመዓቱም ያውካቸዋል።
6እኔ ግን ንጉሤን ሾምሁ በተቀደሰው ተራራዬ በጽዮን ላይ።
7ትእዛዙን እናገራለሁ፤ እግዚአብሔር አለኝ። አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወለድሁህ።
8ለምነኝ፥ አሕዛብን ለርስትህ የምድርንም ዳርቻ ለግዛትህ እሰጥሃለሁ።
9በብረት በትር ትጠብቃቸዋለህ፥ እንደ ሸክላ ሠሪ ዕቃዎች ትቀጠቅጣቸዋለህ።
10አሁንም እናንት ነገሥታት፥ ልብ አድርጉ፤ እናንት የምድር ፈራጆችም፥ ተገሠጹ።
11ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ፥ በረዓድም ደስ ይበላችሁ።
12ተግሣጹን ተቀበሉ ጌታ እንዳይቈጣ እናንተም በመንገድ እንዳትጠፉ፥ ቍጣው ፈጥና ትነድዳለችና። በእርሱ የታመኑ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው።