English

ምዕራፍ 25

1አቤቱ፥ ወደ አንተ ነፍሴን አነሣለሁ።
2አምላኬ፥ አንተን ታመንሁ፤ አልፈር፥ ጠላቶቼ በእኔ አይሣቁብኝ።
3አንተን ተስፋ የሚያደርጉ አያፍሩም፤ በከንቱ የሚገበዙ ያፍራሉ።
4አቤቱ፥ መንገድህን አመልክተኝ፥ ፍለጋህንም አስተምረኝ።
5አንተ የመድኃኒቴ አምላክ ነህና በእውነትህ ምራኝ፥ አስተምረኝም፤ ቀኑን ሁሉ አንተን ተስፋ አድርጌአለሁ።
6አቤቱ፥ ምሕረትህንና ቸርነትህን አስብ፥ ከጥንት ጀምሮ ናቸውና።
7የልጅነቴን ኃጢአትና መተላለፍ አታስብብኝ፤ አቤቱ፥ ስለ ቸርነትህ ብዛት እንደ ምሕረትህ አስበኝ።
8እግዚአብሔር ቸር ቅንም ነው፤ ስለዚህ ኃጢአተኞችን በመንገድ ይመራቸዋል።
9ገሮችን በፍርድ ይመራል፥ ለገሮችም መንገድን ያስተምራቸዋል።
10የእግዚአብሔር መንገድ ሁሉ ቸርነትና እውነት ነው። ቃል ኪዳኑንና ምስክሩን ለሚጠብቁ።
11አቤቱ፥ ኃጢአቴ እጅግ ነውና ስለ ስምህ ይቅር በለኝ።
12እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ማን ነው? በሚመርጠው መንገድ ያስተምረዋል።
13ነፍሱ በመልካም ታድራለች፥ ዘሩም ምድርን ይወርሳል።
14እግዚአብሔር ለሚፈሩት ኃይላቸው ነው፥ ቃል ኪዳኑንም ያስታውቃቸዋል።
15እርሱ እግሮቼን ከወጥመድ ያወጣቸዋልና ዓይኖቼ ሁልጊዜ ወደ እግዚአብሔር ናቸው።
16እኔ ብቻዬንና ችግረኛ ነኝና ፊትህን ወደ እኔ አድርግ ማረኝም።
17የልቤ ችግር ብዙ ነው፤ ከጭንቀቴ አውጣኝ።
18ድካሜንና መከራዬን እይ፥ ኃጢአቴንም ሁሉ ይቅር በለኝ።
19ጠላቶቼ እንደ በዙ እይ፥ የግፍም ጥል ጠልተውኛል።
20ነፍሴን ጠብቅና አድነኝ፤ አንተን ታምኛለሁና አልፈር።
21አንተን ተስፋ አድርጌአለሁና የውሃትና ቅንነት ይጠብቁኝ።
22አቤቱ፥ እስራኤልን ከመከራው ሁሉ አድነው።