English

ምዕራፍ 42

1ዋላ ወደ ውኃ ምንጭ እንደሚናፍቅ፥ አቤቱ፥ እንዲሁ ነፍሴ ወደ አንተ ትናፍቃለች።
2ነፍሴ ወደ ሕያው አምላክ ተጠማች፤ መቼ እደርሳለሁ? የአምላክንስ ፊት መቼ አያለሁ?
3ዘወትር። አምላክህ ወዴት ነው? ሲሉኝ እንባዬ በቀንና በሌሊት ምግብ ሆነኝ።
4ይህን ሳስብ ነፍሴ በእኔ ውስጥ ፈሰሰች፥ ወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ምስጋና መኖሪያ ስፍራ እገባለሁና፤ በዓል የሚያደርጉ ሰዎች የደስታና ምስጋና ቃል አሰሙ።
5ነፍሴ ሆይ፥ ለምን ታዝኛለሽ? ለምንስ ታውኪኛለሽ? የፊቴን መድኃኒት አምላኬን አመሰግነው ዘንድ በእግዚአብሔር ታመኚ።
6አምላኬ ሆይ፥ ነፍሴ በእኔ ውስጥ ታወከች፤ ስለዚህ በዮርዳኖስ ምድር በአርሞንኤምም በታናሹ ተራራ አስብሃለሁ።
7በፍዋፍዋቴህ ድምፅ ቀላይ ቀላይን ትጠራታለች፤ ማዕበልህና ሞገድህ ሁሉ በላዬ አለፈ።
8እግዚአብሔር በቀን ቸርነቱን ያዝዛል፥ በሌሊትም ዝማሬው በእኔ ዘንድ ይሆናል፤ የእኔ ስእለት ለሕይወቴ አምላክ ነው።
9እግዚአብሔርን። አንተ መጠጊያዬ ነህ፤ ለምን ረሳኸኝ? ጠላቶቼ ሲያስጨንቁኝ ለምን አዝኜ እመላለሳለሁ? እለዋለሁ።
10ጠላቶቼ ሁልጊዜ። አምላክህ ወዴት ነው? ባሉኝ ጊዜ አጥንቶቼን እየቀለጣጠሙ ሰደቡኝ።
11ነፍሴ ሆይ፥ ለምን ታዝኛለሽ? ለምንስ ታውኪኛለሽ? የፊቴን መድኃኒት አምላኬን አመሰግነው ዘንድ በእግዚአብሔር ታመኚ።