ምዕራፍ 63
1አምላኬ፥ አምላኬ፥ ወደ አንተ እገሠግሣለሁ፤ ነፍሴ አንተን ተጠማች፥ ሥጋዬ አንተን እንዴት ናፈቀች እንጨትና ውኃ በሌለበት በምድረ በዳ።
2ኃይልህንና ክብርህን አይ ዘንድ እንዲሁ በመቅደስ ውስጥ ተመለከትሁህ።
3ምሕረትህ ከሕይወት ይሻላልና ከንፈሮቼ ያመሰግኑሃል።
4እንዲህ በሕይወቴ ዘመን አመሰግንሃለሁ፥ በአንተም ስም እጆቼን አነሣለሁ።
5ነፍሴ በቅቤና በስብ እንደሚጠግቡ ትጠግባለች፥ ከንፈሮቼም ስምህን በደስታ ያመሰግናሉ።
6በመኝታዬም አስብሃለሁ፥ በማለዳም እናገርልሃለሁ፤
7ረዳቴ ሆነኸኛልና፥ በክንፎችህም ጥላ ደስ ይለኛልና።
8ነፍሴ በኋላህ ተከታተለች፥ እኔንም ቀኝህ ተቀበለችኝ።
9እነርሱ ግን ነፍሴን ለከንቱ ፈለጓት፤ ወደ ምድር ጥልቅ ይገባሉ።
10ለሰይፍ እጅ አልፈው ይሰጣሉ፥ የቀበሮም እድል ፈንታ ይሆናሉ።
11ንጉሥ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለዋል፤ በእርሱ የሚምል ሁሉ ይከብራል፥ ሐሰትን የሚናገር አፍ ይዘጋልና።