English

ምዕራፍ 65

1አቤቱ፥ በጽዮን ለአንተ ምስጋና ይገባል፥ ለአንተም ጸሎት ይቀርባል።
2ሥጋ ሁሉ ጸሎትን ወደምትሰማ ወደ አንተ ይመጣል።
3የዓመፃ ነገር በረታብን፤ ኃጢአታችንንስ አንተ ይቅር ትላለህ።
4አንተ የመረጥኸው በአደባባዮችህም ለማደር የተቀበልኸው ምስጉን ነው፤ ከቤትህ በረከት እንጠግባለን።
5ቤተ መቅደስህ ቅዱስ ነው በጽድቅም ድንቅ ነው። በምድር ዳርቻ ሁሉና በሩቅ ባሕር ውስጥ ላሉ ተስፋቸው የሆንህ፥ አምላካችንና መድኃኒታችን ሆይ፥ ስማን።
6በጉልበትህ ተራሮችን አጸናሃቸው፥ በኃይልም ታጥቀሃል።
7የባሕሩን ጥልቀት የሞገድንም ጩኸት ታናውጣለህ።
8ከተአምራትህ የተነሣ አሕዛብ ይደነግጣሉ፥ በምድር ዳርቻም የሚኖሩ ይፈራሉ፤ የጥዋትንና የማታን መውጫ ደስ ታሰኛቸዋለህ።
9ምድርን ጐበኘሃት አጠጣሃትም፥ ብልጥግናዋንም እጅግ አበዛህ፤ የእግዚአብሔርን ወንዝ ውኃን የተመላ ነው፤ ምግባቸውን አዘጋጀህ እንዲሁ ታሰናዳለህና።
10ትልምዋን ታረካለህ፥ ቦይዋንም ታስተካክላለህ፤ በነጠብጣብ ታለሰልሳታለህ፥ ቡቃያዋንም ትባርካለህ።
11በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ፥ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል።
12የምድረ በዳ ተራሮች ይረካሉ፥ ኮረብቶችም በደስታ ይታጠቃሉ።
13ማሰማርያዎች መንጎችን ለበሱ፥ ሸለቆችም በእህል ተሸፈኑ፤ በደስታ ይጮኻሉ ይዘምራሉም።