English

ምዕራፍ 7

1አቤቱ አምላኬ፥ በአንተ ታመንሁ፤ ከሚያሳድዱኝ ሁሉ አድነኝና አውጣኝ፥
2ነፍሴን እንደ አንበሳ ነጥቀው እንዳይሰብሩዋት፥ የሚያድንና የሚታደግ ሳይኖር።
3አቤቱ አምላኬ፥ እንዲህስ ካደረግሁ፥ ዓመፃም በእጄ ቢኖር፥
4ክፉ ላደረጉብኝም ክፉን መልሼላቸው ብሆን፥ ጠላቴንም በከንቱ ገፍቼው ብሆን፥
5ጠላት ነፍሴን ያሳድዳት ያግኛትም፥ ሕይወቴንም በምድር ላይ ይርገጣት፥ ክብሬንም በትቢያ ላይ ያዋርዳት።
6አቤቱ፥ በመዓትህ ተነሥ፥ በጠላቶቼ ላይ በቍጣ ተነሣባቸው፤ አቤቱ አምላኬ፥ ባዘዝኸው ትእዛዝ ንቃ።
7የአሕዛብም ጉባኤ ይከብብሃል፥ በእነርሱም ላይ ወደ ከፍታ ተመለስ።
8እግዚአብሔር በአሕዛብ ይፈርዳል፤ አቤቱ፥ እንደ ጽድቄ ፍረድልኝ፥ እንደ የዋህነቴም ይሁንልኝ።
9የኃጥኣን ክፋት ይጥፋ፥ ጻድቁን ግን አቅና፤ እግዚአብሔር ልቡናንና ኵላሊትን ይመረምራል።
10እግዚአብሔር የጽድቅ ጋሻዬ ነው ልበ ቅኖችን የሚያድናቸው።
11እግዚአብሔር የእውነት ዳኛ ነው፥ ኃይለኛም ታጋሽም ነው፥ ሁልጊዜም አይቈጣም።
12ባትመለሱ ግን ሰይፉን ይስላል፥ ቀስቱን ገተረ አዘጋጀም፤
13የሞት መሣርያንም አዘጋጀበት፥ ፍላጻዎቹንም የሚቃጠሉ አደረገ።
14እነሆ፥ በዓመፃ ተጨነቀ ጉዳትን ፀነሰ ኃጢአትንም ወለደ።
15ጕድጓድን ማሰ ቈፈረም። ባደረገውም ጕድጓድ ይወድቃል።
16ጉዳቱ በራሱ ይመለሳል፥ ዓመፃውም በአናቱ ላይ ትወርዳለች።
17እግዚአብሔርን እንደ ጽድቁ መጠን አመሰግናለሁ፥ ለልዑል እግዚአብሔርም ስም እዘምራለሁ።