ምዕራፍ 9
1አቤቱ፥ በልቤ ሁሉ አመሰግንሃለሁ፥ ተአምራትህንም ሁሉ እነግራለሁ።
2በአንተ ደስ ይለኛል፥ ሐሤትንም አደርጋለሁ፤ ልዑል ሆይ፥ ለስምህ እዘምራለሁ።
3ጠላቶቼ ወደ ኋላ በተመለሱ ጊዜ፥ ይሰናከላሉ ከፊትህም ይጠፋሉ።
4ፍርዴንና በቀሌን አድርገህልኛልና፤ ጽድቅን እየፈረድህ በዙፋንህ ላይ ተቀመጥህ።
5አሕዛብን ገሠጽህ፥ ዝንጉዎችንም አጠፋህ፥ ስማቸውንም ለዘላለም ደመሰስህ።
6ጠላቶች በጦር ለዘላለም ጠፉ፥ ከተሞቻቸውንም አፈረስህ፥ ዝክራቸውም በአንድነት ጠፋ።
7እግዚአብሔር ግን ለዘላለም ይኖራል፥ ዙፋኑንም ለመፍረድ አዘጋጀ፤
8እርሱም ዓለምን በጽድቅ ይፈርዳታል፥ አሕዛብንም በቅንነት ይዳኛቸዋል።
9እግዚአብሔርም ለድሆች መጠጊያ ሆናቸው፥ እርሱም በመከራቸው ጊዜ ረዳታቸው ነው።
10ስምህን የሚያውቁ ሁሉ በአንተ ይታመናሉ፥ አቤቱ፥ የሚሹህን አትተዋቸውምና።
11በጽዮን ለሚኖር ለእግዚአብሔር ዘምሩ፥ በአሕዛብም መካከል አደራረጉን ንገሩ፤
12ደማቸውን የሚመራመር እርሱ አስቦአልና፥ የድሆችንም ጩኸት አልረሳምና።
13አቤቱ፥ እዘንልኝ፥ ጠላቶቼም የሚያመጡብኝን መከራ እይ፥ ከሞት ደጆች ከፍ ከፍ የምታደርገኝ፤
14ምስጋናውን ሁሉ እናገር ዘንድ፤ በጽዮን ልጅ በደጆችዋ በማዳንህ ደስ ይለኛል።
15አሕዛብ በሠሩት ጕድጓድ ወደቁ፥ በዚያችም በሸሸጓት ወጥመድ እግራቸው ተጠመደች።
16እግዚአብሔር ፍርድን በማድረግ የታወቀ ነው፤ ኃጢአተኛው በእጆቹ ሥራ ተጠመደ።
17ኃጢአተኞች ወደ ሲኦል ይመለሳሉ፥ እግዚአብሔርን የሚረሱ አሕዛብም ሁሉ።
18ድሀ ለዘላለም አይረሳምና፥ የችግረኞችም ተስፋቸው ለዘላለም አይጠፋም።
19አቤቱ፥ ተነሥ፤ ሰውም አይበርታ፥ አሕዛብም በፊትህ ይፈረድባቸው።
20አቤቱ፥ ፍርሃትን በላያቸው ጫንባቸው፤ አሕዛብ ሰዎች እንደ ሆኑ ይወቁ።