ምዕራፍ 92
1እግዚአብሔርን ማመስገን መልካም ነው፥ ልዑል ሆይ፥ ለስምህም ዝማሬ ማቅረብ፤
2በማለዳ ምሕረትን፥ በሌሊትም እውነትህን ማውራት
3አሥር አውታር ባለው በበገና፥ ከምስጋና ጋርም በመሰንቆ።
4አቤቱ፥ በሥራህ ደስ አሰኝተኸኛልና፤ በእጅህም ሥራ ደስ ይለኛልና።
5አቤቱ፥ ሥራህ እጅግ ትልቅ ነው፥ አሳብህም እጅግ ጥልቅ ነው።
6ሰነፍ ሰው አያውቅም። ልብ የሌለውም ይህን አያስተውለውም።
7ኃጢአተኞች እንደ ሣር ሲበቅሉ ዓመፃ የሚያደርጉ ሁሉ ሲለመልሙ፥ ለዘላለም ዓለም እንዲጠፋ ነው።
8አቤቱ፥ አንተ ግን ለዘላለም ልዑል ነህ፤
9አቤቱ፥ እነሆ፥ ጠላቶችህ ይጠፋሉና፥ ዓመፃንም የሚሠሩ ሁሉ ይበተናሉና።
10ቀንዴ አንድ ቀንድ እንዳለው ከፍ ከፍ ይላል፤ ሽምግልናዬም በዘይት ይለመልማል።
11ዓይኔም በጠላቶቼ ላይ አየች፥ ጆሮዬም በእኔ ላይ በቆሙ በክፉዎች ላይ ሰማች።
12ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል፥ እንደ ሊባኖስ ዝግባም ያድጋል።
13በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ተተክለዋል፥ በአምላካችንም አደባባይ ውስጥ ይበቅላሉ።
14ያን ጊዜ በለመለመ ሽምግልና ያፈራሉ ደስተኞችም ሆነው ይኖራሉ።
15አምላኬ እግዚአብሔር እውነተኛ እንደ ሆነ ይነግራሉ፥ በእርሱም ዘንድ ዓመፃ የለም።