ምዕራፍ 99
1እግዚአብሔር ነገሠ፥ አሕዛብ ይደንግጡ፤ በኪሩቤል ላይ ተቀመጠ፥ ምድር ትናወጥ።
2እግዚአብሔር በጽዮን ታላቅ ነው፤ እርሱም በአሕዛብ ሁሉ ላይ ከፍ ከፍ አለ።
3ግሩምና ቅዱስ ነውና ሁሉ ታላቅ ስምህን ያመስግኑ።
4የንጉሥ ክብር ፍርድን ይወድዳል፤ አንተ ቅንነትን አጸናህ፥ ለያዕቆብ ፍርድንና ጽድቅን አንተ አደረግህ።
5አምላካችንን እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ አድርጉት፥ ቅዱስ ነውና ወደ እግሩ መረገጫ ስገዱ።
6ሙሴና አሮን በካህናቱ ዘንድ፥ ሳሙኤልም ስሙን በሚጠሩት ዘንድ ናቸው። እግዚአብሔርን ጠሩት፥ እርሱም መለሰላቸው።
7በደመና ዓምድም ተናገራቸው፤ ምስክሩንና የሰጣቸውን ትእዛዝ ጠበቁ።
8አቤቱ አምላክችን ሆይ፥ አንተ ሰማሃቸው፤ አቤቱ፥ አንተ ማርሃቸው፥ ሥራቸውን ሁሉ ግን ተበቀልሃቸው።
9አምላካችንን እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ አድርጉት፥ በቅዱስ ተራራውም ስገዱ፤ አምላካችን እግዚአብሔር ቅዱስ ነውና።