English

ምዕራፍ 6

1የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ ሠሩ፤ እግዚአብሔርም በምድያም እጅ ሰባት ዓመት አሳልፎ ሰጣቸው።
2የምድያምም እጅ በእስራኤል ላይ ጠነከረች፤ ከምድያምም የተነሣ የእስራኤል ልጆች በተራራ ላይ ጕድጓድና ዋሻ ምሽግም አበጁ።
3እስራኤልም ዘር በዘሩ ጊዜ ምድያማውያን አማሌቃውያንም በምሥራቅም የሚኖሩ ሰዎች ይመጡባቸው ነበር፤
4በእነርሱም ላይ ይሰፍሩ ነበር፥ እስከ ጋዛም ድረስ የምድሩን ቡቃያ ያጠፉ ነበር፥ ምግብንም ለእስራኤል አይተዉም ነበር፤ በግ ወይም በሬ ወይም አህያ ቢሆን አይተዉም።
5እንስሶቻቸውንና ድንኳኖቻቸውን ይዘው በብዛት እንደ አንበጣ ሆነው ይመጡ ነበር፤ ለእነርሱና ለግመሎቻቸውም ቍጥር አልነበራቸውም፤ ምድሪቱንም ያጠፉ ዘንድ ይመጡ ነበር።
6ከምድያምም የተነሣ እስራኤል እጅግ ተጠቁ፤ የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጮኹ።
7እንዲህም ሆነ፤ የእስራኤል ልጆች በምድያም ምክንያት ወደ እግዚአብሔር በጮኹ ጊዜ፥
8እግዚአብሔር ወደ እስራኤል ልጆች ነቢይ ላከ፥ እርሱም አለ። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ ከግብፅ ምድር አወጣኋችሁ፥ ከባርነትም ቤት አስለቀቅኋችሁ፤
9ከግብፃውያንም እጅ፥ ከሚጋፉአችሁም ሁሉ እጅ አዳንኋችሁ፥ ከፊታችሁም አሳደድኋቸው፥ አገራቸውንም ሰጠኋችሁ፤
10እናንተንም። እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነኝ፤ በምድራቸው የተቀመጣችሁባቸውን የአሞራያውያንን አማልክት አትፍሩ አልኋችሁ። እናንተ ግን ድምፄን አልሰማችሁም።
11የእግዚአብሔርም መልአክ መጥቶ በዖፍራ ባለችው ለአቢዔዝራዊው ለኢዮአስ በነበረችው በአድባሩ ዛፍ በታች ተቀመጠ፤ ልጁም ጌዴዎን ከምድያማውያን ለመሸሸግ በወይን መጥመቂያው ውስጥ ስንዴ ይወቃ ነበር።
12የእግዚአብሔርም መልአክ ለእርሱ ተገልጦ። አንተ ጽኑዕ ኃያል ሰው፥ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው አለው።
13ጌዴዎንም። ጌታዬ ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ነገር ሁሉ ለምን ደረሰብን? አባቶቻችንስ። እግዚአብሔር ከግብፅ አውጥቶናል ብለው ይነግሩን የነበረ ተአምራቱ ወዴት አለ? ወዴት አለ? አሁን ግን እግዚአብሔር ትቶናል፥ በምድያማውያንም እጅ አሳልፎ ሰጥቶናል አለው።
14እግዚአብሔርም ወደ እርሱ ዘወር ብሎ። በዚህ በጕልበትህ ሂድ፥ እስራኤልንም ከምድያም እጅ አድን፤ እነሆ፥ ልኬሃለሁ አለው።
15እርሱም። ጌታ ሆይ፥ እስራኤልን በምን አድናለሁ? ወገኔ ከምናሴ ነገድ ከሁሉ ይልቅ የተጠቃ ነው፤ እኔም በአባቴ ቤት የሁሉ ታናሽ ነኝ አለው።
16እግዚአብሔርም። በእርግጥ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ ምድያምንም እንደ አንድ ሰው አድርገህ ትመታለህ አለው።
17እርሱም። በአንተ ዘንድ ሞገስ ካገኘሁ፥ የምትናገረኝም አንተ እንደ ሆንህ ምልክት አሳየኝ፤
18ወደ አንተም እስክመለስ ድረስ፥ ቍርባኔንም አምጥቼ እስካቀርብልህ ድረስ፥ እባክህ፥ ከዚህ አትላወስ አለው። እርሱም። እስክትመለስ ድረስ እቆያለሁ አለ።
19ጌዴዎን ገባ የፍየሉንም ጠቦት የኢፍ መስፈሪያም ዱቄት የቂጣ እንጎቻ አዘጋጀ፤ ሥጋውን በሌማት አኖረ፥ መረቁንም በምንቸት ውስጥ አደረገ፥ ሁሉንም ይዞ በአድባሩ ዛፍ በታች አቀረበለት።
20የእግዚአብሔርም መልአክ። ሥጋውንና የቂጣውን እንጎቻ ወስደህ በዚህ ድንጋይ ላይ አኑር፥ መረቁንም አፍስስ አለው። እንዲሁም አደረገ።
21የእግዚአብሔርም መልአክ በእጁ ያለውን የበትሩን ጫፍ ዘርግቶ ሥጋውንና የቂጣውን እንጎቻ አስነካ፤ እሳትም ከድንጋዩ ውስጥ ወጥቶ ሥጋውንና የቂጣውን እንጎቻ በላ። የእግዚአብሔርም መልአክ ከዓይኑ ተሰወረ።
22ጌዴዎንም የእግዚአብሔር መልአክ እንደ ሆነ አየ፤ ጌዴዎንም። አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ ወዮልኝ፤ የእግዚአብሔርን መልአክ ፊት ለፊት አይቻለሁና አለ።
23እግዚአብሔርም። ሰላም ለአንተ ይሁን፤ አትፍራ፤ አትሞትም አለው።
24ጌዴዎንም በዚያ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፥ ስሙንም። እግዚአብሔር ሰላም ብሎ ጠራው። እርሱም እስከ ዛሬ ድረስ ለአቢዔዝራውያን በምትሆነው በዖፍራ አለ።
25እግዚአብሔርም በዚያ ሌሊት። የአባትህን በሬ፥ ሰባት ዓመት የሆነውን ሁለተኛውን በሬ፥ ውሰድ፥ የአባትህ የሆነውንም የበኣል መሠዊያ አፍርስ፥ በእርሱም ዙሪያ ያለውን የማምለኪያ ዐፀድ ቍረጥ፤
26በዚያም ኮረብታ አናት ላይ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር መሠዊያ አሳምረህ ሥራ ሁለተኛውንም በሬ ውሰድ፥ በዚያም በቈረጥኸው በማምለኪያ ዐፀዱ እንጨት ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቅርብ አለው።
27ጌዴዎንም ከባሪያዎቹ አሥር ሰዎችን ወስዶ እግዚአብሔር እንዳለው አደረገ፤ የአባቱን ቤተ ሰቦች የከተማውንም ሰዎች ስለ ፈራ ይህን በቀን ለማድረግ አልቻለም፥ ነገር ግን በሌሊት አደረገው።
28የከተማውም ሰዎች ማልደው ተነሡ፥ እነሆም፥ የበኣል መሠዊያ ፈርሶ፥ በዙሪያው ያለውም የማምለኪያ ዐፀድ ተቈርጦ፥ በተሠራውም መሠዊያ ላይ ሁለተኛው በሬ ተሠውቶ አገኙት።
29እርስ በርሳቸውም። ይህን ነገር ያደረገ ማን ነው? ተባባሉ። በጠየቁና በመረመሩም ጊዜ። ይህን ነገር ያደረገ የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን ነው አሉ።
30የከተማውም ሰዎች ኢዮአስን። የበኣልን መሠዊያ አፍርሶአልና፥ በዙሪያውም ያለውን የማምለኪያ ዐፀድ ቈርጦአልና እንዲሞት ልጅህን አውጣ አሉት።
31ኢዮአስም እርሱን የተቃወሙትን ሁሉ። ለበኣል ትምዋገቱለታላችሁን? ወይስ እርሱን ታድናላችሁን? የሚምዋገትለት ሁሉ እስከ ነገ ይሙት፤ እርሱ አምላክ ከሆነ መሠዊያውን ካፈረሰው ጋር ለራሱ ይምዋገት አላቸው።
32ስለዚህም በዚያ ቀን። መሠዊያውን አፍርሶአልና በኣል ከእርሱ ጋር ይምዋገት ብሎ ጌዴዎንን። ይሩበኣል ብሎ ጠራው።
33ምድያማውያንም አማሌቃውያንም ሁሉ የምሥራቅም ሰዎች አንድ ሆነው ተሰበሰቡ፥ ዮርዳኖስንም ተሻገሩ፥ በኢይዝራኤልም ሸለቆ ሰፈሩ።
34የእግዚአብሔርም መንፈስ በጌዴዎን ገባበት፥ እርሱም ቀንደ መለከቱን ነፋ፤ የአቢዔዝርም ሰዎች ተጠርተው በኋላው ተከተሉት።
35ወደ ምናሴም ነገድ ሁሉ መልክተኞችን ሰደደ እነርሱም ደግሞ ተጠርተው በኋላው ተከተሉት፤ መልክተኞችንም ወደ አሴርና ወደ ዛብሎን ወደ ንፍታሌምም ሰደደ፥ እነርሱም ሊገናኙአቸው ወጡ።
36ጌዴዎንም እግዚአብሔርን። እንደ ተናገርህ የእስራኤልን ልጆች በእኔ እጅ ታድን እንደ ሆነ፥
37እነሆ፥ በአውድማው ላይ የተባዘተ የበግ ጠጕር አኖራለሁ፤ በጠጕሩ ብቻ ላይ ጠል ቢሆን በምድሩም ሁሉ ደረቅ ቢሆን፥ እንደ ተናገርህ የእስራኤልን ልጆች በእኔ እጅ እንድታድናቸው አውቃለሁ አለ።
38እንዲሁም ሆነ፤ በነጋውም ማልዶ ተነሣ፥ ጠጕሩንም ጨመቀው፥ ከጠጕሩም የተጨመቀው ጠል ቆሬ ሙሉ ውኃ ሆነ።
39ጌዴዎንም እግዚአብሔርን። እኔ ይህን አንድ ጊዜ ስናገር አትቈጣኝ፤ እኔ ይህን አንድ ጊዜ በጠጕሩ፥ እባክህ፥ ልፈትን፤ አሁንም በጠጕሩ ብቻ ላይ ደረቅ ይሁን፥ በምድሩም ሁሉ ላይ ጠል ይሁን አለው።
40እግዚአብሔርም በዚያ ሌሊት እንዲሁ አደረገ፤ በጠጕሩ ብቻ ላይ ደረቅ ነበረ፥ በምድሩም ሁሉ ላይ ጠል ነበረ።