English

ምዕራፍ 17

1ጥል ባለበት ዘንድ እርድ ከሞላበት ቤት በጸጥታ ደረቅ ቍራሽ ይሻላል።
2አስተዋይ ባሪያ ነውረኛውን ልጅ ይገዛል፥ በወንድማማች መካከልም ርስትን ይካፈላል።
3ማቅለጫ ለብር፥ ከውር ለወርቅ ነው፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ይፈትናል።
4ክፉ ሰው የበደለኛን ከንፈር ይሰማል፤ ሐሰተኛም ወደ ተንኰለኛ ምላስ ያደምጣል።
5በድሀ የሚያላግጥ ፈጣሪውን ይሰድባል፤ በጥፋትም ደስ የሚለው ሳይቀጣ አይቀርም።
6የሽማግሌዎች አክሊል የልጅ ልጆች ናቸው፤ የልጆችም ክብር አባቶቻቸው ናቸው።
7ለሰነፍ የኵራት አነጋገር አይገባውም፤ ይልቁንም ሐሰተኛ ከንፈር ለመኰንን አይገባውም።
8ገንዘብ ባደረገው ፊት መማለጃ እንደ ተዋበ ዕንቍ ነው፥ ወደ ዞረበትም ስፍራ ሁሉ ሥራውን ያቀናል።
9ኃጢአትን የሚከድን ሰው ፍቅርን ይሻል፤ ነገርን የሚደጋግም ግን የተማመኑትን ወዳጆቹን ይለያያል።
10መቶ ግርፋት በሰነፍ ጠልቆ ከሚገባ ይልቅ ተግሣጽ በአስተዋይ ሰው ጠልቆ ወደ ልቡ ይገባል።
11ክፉ ሰው ዓመፃን ብቻ ይሻል፤ ስለዚህ ጨካኝ መልአክ ይላክበታል።
12ሰነፍን በስንፍናው ከመገናኘት ልጆችዋ የተነጠቁባትን ድብ መገናኘት ይሻላል።
13በመልካም ፋንታ ክፉን የሚመልስ፥ ክፉ ነገር ከቤቱ አትርቅም።
14የጠብ መጀመሪያ እንደ ውኃ አፈሳሰስ ነው፤ ስለዚህ ጠብ ሳይበረታ አንተ ክርክርን ተው።
15ኀጥኡን የሚያጸድቅና በጻድቁ ላይ የሚፈርድ፥ ሁለቱ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊዎች ናቸው።
16በሰነፍ እጅ የጥበብ መግዣ ገንዘብ መኖሩ ስለ ምንድር ነው? ጥበብን ይገዛ ዘንድ አእምሮ የለውምና።
17ወዳጅ በዘመኑ ሁሉ ይወድዳል፤ ወንድምም ለመከራ ይወለዳል።
18አእምሮ የጐደለው ሰው አጋና ይመታል፥ በባልንጀራውም ፊት ይዋሳል።
19ዓመፃን የሚወድድ ክርክርን ይወድዳል፤ ደጁንም ዘለግ የሚያደርግ ውድቀትን ይሻል።
20ጠማማ ልብ ያለው መልካምን አያገኝም፥ ምላሱንም የሚገለብጥ በክፉ ላይ ይወድቃል።
21ሰነፍን የሚወልድ ኀዘን ይሆንበታል፥ የደንቆሮ ልጅም አባት ደስ አይለውም።
22ደስ ያላት ልብ መልካም መድኃኒት ናት፤ ያዘነች ነፍስ ግን አጥንትን ታደርቃለች።
23ኀጥእ የፍርድን መንገድ ለማጥመም ከብብት መማለጃን ይወስዳል።
24በአስተዋይ ፊት ጥበብ ትኖራለች፤ የሰነፍ ዓይን ግን በምድር ዳርቻ ነው።
25ሰነፍ ልጅ ለአባቱ ፀፀት ነው፥ ለወለደችውም ምሬት ነው።
26ጻድቅን መቅጣት፥ ጨዋ ሰውንም በጻድቅነቱ መምታት መልካም አይደለም።
27ጥቂት ቃልን የሚናገር አዋቂ ነው፥ መንፈሱም ቀዝቃዛ የሆነ አስተዋይ ነው።
28ሰነፍ ዝም ቢል ጠቢብ ሆኖ ይቈጠራል፥ ከንፈሩንም የሚቈልፍ። ባለ አእምሮ ነው ይባላል።