ምዕራፍ 24
1ልጄ ሆይ፥ በክፉ ሰዎች አትቅና፥ ከእነርሱ ጋርም መሆንን አትውደድ፤
2ልባቸው ግፍን ታስባለችና፥ ከንፈራቸውም ሽንገላን ትናገራለችና።
3ቤት በጥበብ ይሠራል፥ በማስተዋልም ይጸናል።
4በእውቀት ከከበረውና ካማረው ሀብት ሁሉ ጓዳዎች ይሞላሉ።
5ጠቢብ ሰው ብርቱ ነው፥ አዋቂም ሰው ኃይሉን ያበዛል።
6በመልካም ሥርዓት ሰልፍ ታደርጋለህ፤ ድልም ብዙ ምክር ባለበት ዘንድ ነው።
7ጥበብ ለሰነፍ ከፍ ብላ የራቀች ናት፤ በበርም አፉን አይከፍትም።
8ክፉ ለማድረግ የሚያስብ ተንኰለኛ ይባላል።
9የስንፍና ሐሳብ ኃጢአት ነው፤ ሰዎች ፌዘኛውን ይጸየፉታል።
10በመከራ ቀን ብትላላ ጉልበትህ ጥቂት ነው።
11ወደ ሞት የሚነዱትን ታደግ፤ ሊታረዱ የተወሰኑትን አድን።
12እነሆ፥ ይህን አላወቀውም ብትል፥ ልቦችን የሚመረምር እርሱ አያስተውልምን? ነፍስህንም የሚመለከት እርሱ አያውቅምን? ለሰውስ ሁሉ እንደ ሥራው አይመልስለትምን?
13ልጄ ሆይ፥ መልካም ነውና ማር ብላ፤ ወለላም ለጣምህ ጣፋጭ ነው።
14ጥበብም ለነፍስህ እንዲሁ እንደሚሆን እወቅ፤ ብታገኘውም ፍጻሜህ መልካም ይሆናል፥ ተስፋህም አይጠፋም።
15እንደ ኀጥእ በጻድቅ ቤት ላይ አትሸምቅ፤ ማደሪያውንም አታውክ።
16ጻድቅ ሰባት ጊዜ ይወድቃልና፥ ይነሣማል፤ ኀጥኣን ግን በክፉ ላይ ይወድቃሉ።
17ጠላትህ ቢወድቅ ደስ አይበልህ፥ በመሰናከሉም ልብህ ሐሤት አያድርግ፥
18እግዚአብሔር ያንን አይቶ በዓይኑ ክፉ እንዳይሆን፥ ቍጣውንም ከእርሱ እንዳይመልስ።
19ስለ ኃጢአተኞች አትቈጣ፥ በክፉዎችም አትቅና።
20ለኃጢአተኛ የፍጻሜ ተስፋ የለውምና፥ የኅጥኣንም መብራት ይጠፋልና።
21ልጄ ሆይ፥ እግዚአብሔርንና ንጉሥን ፍራ፥ ከዓመፀኞችም ጋር አትደባለቅ።
22መከራቸው ድንገት ይነሣልና፤ ከሁለቱ የሚመጣውን ጥፋት ማን ያውቃል? ፍን [የሚቀጥለው ከግሪክ የተጨመረ ነው።] የነገሩትን የሚሰማ ልጅ ከጥፋት የራቀ ነው፤ የነገሩትን የሚቀበልን ሰው እግዚአብሔር ይቀበለዋል። ከንጉሥ አንደበት ምንምን ሐሰት ይነገራል አይባልም፤ ከአንደበቱም የሚወጣ ሐሰት የለም። የንጉሥ ቃል ሾተል ናት፤ ለጥፋት የተሰጠችውን ሰው ሰውነት ታጠፋዋለች እንጂ አንድ አካል ብቻ የምታጠፋ አይደለም። ሰይፍ መዓቱ ብትሳል ግን ከወገኑ ጋር ሰውን ታጠፋለች፤ ከአሞሮች ግልገል ወገን የማይበላ እስኪሆን ድረስ እንደ እሳት ነበልባል ታቃጥላለች።
23እነዚህ ደግሞ የጠቢባን ቃሎች ናቸው። በፍርድ ታደላ ዘንድ መልካም አይደለም።
24ኀጥኡን። ጻድቅ ነህ የሚለውን ወገኖች ይረግሙታል አሕዛብም ይጠሉታል፤
25የሚዘልፉት ግን ደስታ ይሆንላቸዋል፥ በላያቸውም መልካም በረከት ትመጣላቸዋለች።
26በቀና ነገር የሚመልስ ከንፈርን ይስማል።
27በስተ ሜዳ ሥራህን አሰናዳ፥ ስለ አንተ በእርሻ አዘጋጃት፤ ከዚያም በኋላ ቤትህን ሥራ።
28በባልንጀራህ ላይ በከንቱ ምስክር አትሁን፥ በከንፈርህም አታባብለው።
29እንዳደረገብኝ እንዲሁ አደርግበታለሁ፥ እንደ ሥራውም እመልስበታለሁ አትበል።
30በታካች ሰው እርሻ፥ አእምሮ በጐደለውም ሰው ወይን ቦታ አለፍሁ።
31እነሆም፥ ሁሉ እሾህ ሞልቶበታል፥ ፊቱንም ሳማ ሸፍኖታል፥ የድንጋዩም ቅጥር ፈርሶአል።
32ተመለከትሁና አሰብሁ፤ አየሁትና ተግሣጽን ተቀበልሁ።
33ጥቂት ትተኛለህ፥ ጥቂትም ታንቀላፋለህ፥ ትተኛም ዘንድ ጥቂት እጅህን ታጥፋለህ፤
34እንግዲህ ድህነትህ እንደ ወንበዴ፥ ችጋርህም ሰይፍ እንደ ታጠቀ ሰው ይመጣብሃል። [በግዕዝ መጽሐፈ ተግሣጽ ይባላል]