English

ምዕራፍ 26

1በረዶ በበጋ ዝናብም በመከር እንዳይገባ፥ እንዲሁ ለሰነፍ ክብር አይገባውም።
2እንደሚተላለፍ ድንቢጥ ወዲያና ወዲህም እንደሚበርር ጨረባ፥ እንዲሁ ከንቱ እርግማን በማንም ላይ አይደርስም።
3አለንጋ ለፈረስ፥ ልጓም ለአህያ፥ በትርም ለሰነፍ ጀርባ ነው።
4አንተ ደግሞ እርሱን እንዳትመስል ለሰነፍ እንደ ስንፍናው አትመልስለት።
5ለራሱ ጠቢብ የሆነ እንዳይመስለው ለሰነፍ እንደ ስንፍናው መልስለት።
6በሰነፍ መልእክተኛ እጅ ነገርን የሚልክ እግሮቹን ይቈርጣል ግፍንም ይጠጣል።
7እንደሚንጠለጠሉ የአንካሳ እግሮች፥ እንዲሁም ምሳሌ በሰነፎች አፍ ነው።
8ለሰነፍ ክብርን የሚሰጥ ድንጋይን በወንጭፍ እንደሚያስር ነው።
9እሾህ በስካር እጅ እንደሚሰካ፥ እንዲሁ ምሳሌ በሰነፎች አፍ ነው።
10ዋና ሠራተኛ ሁሉን ነገር ይሠራል፤ ሰነፍን የሚቀጥር ግን መንገድ አላፊውን እንደሚቀጥር ነው።
11ወደ ትፋቱ እንደሚመለስ ውሻ ስንፍናውን የሚደግም ሰው እንዲሁ ነው።
12ለራሱ ጠቢብ የሆነ የሚምስለውን ሰው አየኽውን? ከእርሱ ይልቅ ለሰነፍ ተስፋ አለው።
13ታካች ሰው። አንበሳ በመንገድ አለ፤ አንበሳ በጎዳና አለ ይላል።
14ሣንቃ በማጠፊያው ላይ እንደሚዞር፥ እንዲሁ ታካች ሰው በአልጋው ላይ ይመላለሳል።
15ታካች ሰው እጁን ወደ ወጭት ያጠልቃል፤ ወደ አፉም ይመልሳት ዘንድ ለእርሱ ድካም ነው።
16ታካች ሰው በጥበብ ከሚመልሱ ከሰባት ሰዎች ይልቅ ለራሱ ጠቢብ የሆነ ይመስለዋል።
17አልፎ በሌላው ጥል የሚደባለቅ ውሻን በጅራቱ እንደሚይዝ ነው።
18ትንታግንና ፍላጻን ሞትንም እንደሚወረውር እንደ ዕብድ ሰው፥
19ባልንጀራውን የሚያታልል። በጨዋታ አደረግሁት የሚል ሰውም እንዲሁ ነው።
20እንጨት ባለቀ ጊዜ እሳት ይጠፋል፤ ጆሮ ጠቢ በሌለበትም ዘንድ ጠብ ጸጥ ይላል።
21ከሰል ፍምን እንጨትም እሳትን እንዲያበዛ፥ እንዲሁ ቍጡ ሰው ጠብን ያበዛል።
22የጆሮ ጠቢ ቃል እንደ ጣፋጭ መብል ነው፥ እርሱም እስከ ሆድ ጕርጆች ድረስ ይወርዳል።
23ክፋት በልቡ ሳለ ፍቅርን የሚናገር ከንፈር በብር ዝገት እንደ ተለበጠ የሸክላ ዕቅ ነው።
24ጠላት በከንፈሩ ተስፋ ይሰጣል፥ በልቡ ግን ተንኰልን ያኖራል።
25በልቡ ሰባት ርኵሰት አለበትና በቃሉ አሳምሮ ቢናገርህ አትመነው።
26ጠላትነቱን በተንኰል የሚሸሽግ፥ ክፋቱ በጉባኤ መካከል ይገለጣል።
27ጕድጓድን የሚምስ ይወድቅበታል፤ ድንጋይንም የሚያንከባልል ይገለበጥበታል።
28ሐሰተኛ ምላስ ያቈሰላቸውን ሰዎች ይጠላል፤ ልዝብ አፍም ጥፋትን ያመጣል።