ምዕራፍ 3
1ልጄ ሆይ፥ ሕጌን አትርሳ፥ ልብህም ትእዛዛቴን ይጠብቅ።
2ብዙ ዘመናትና ረጅም ዕድሜ ሰላምም ይጨምሩልሃልና።
3ምሕረትና እውነት ከአንተ አይራቁ፤ በአንገትህ እሰራቸው፤ በልብህ ጽላት ጻፋቸው።
4በእግዚአብሔርና በሰው ፊትም ሞገስንና መልካም ዝናን ታገኛለህ።
5በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤
6በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፥ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል።
7በራስህ አስተያየት ጠቢብ አትሁን፤ እግዚአብሔርን ፍራ፥ ከክፋትም ራቅ፤
8ይህም ለሥጋህ ፈውስ ይሆንልሃል፥ ለአጥንትህም ጠገን።
9እግዚአብሔርን ከሀብትህ አክብር፥ ከፍሬህም ሁሉ በኵራት፤
10ጐተራህም እህልን ይሞላል፥ መጥመቂያህም በወይን ጠጅ ሞልታ ትትረፈረፋለች።
11ልጄ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ተግሣጽ አትናቅ፥ በገሠጸህም ጊዜ አትመረር።
12እግዚአብሔር የወደደውን ይገሥጻልና፥ አባት የሚወድደውን ልጁን እንደሚገሥጽ።
13ጥበብን የሚያገኝ ሰው ምስጉን ነው፥ ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርግ፤
14በወርቅና በብር ከመነገድ ይልቅ በእርስዋ መነገድ ይሻላልና።
15ከቀይ ዕንቍም ትከብራለች፥ የተከበረም ነገር ሁሉ አይተካከላትም።
16በቀኝዋ ረጅም ዘመን ነው፥ በግራዋም ባለጠግነትና ክብር።
17መንገድዋ የደስታ መንገድ ነው፥ ጎዳናዋም ሁሉ ሰላም ነው።
18እርስዋ ለሚይዙአት የሕይወት ዛፍ ናት፥ የተመረኰዘባትም ሁሉ ምስጉን ነው።
19እግዚአብሔር በጥበብ ምድርን መሠረተ፥ በማስተዋልም ሰማያትን አጸና።
20በእውቀቱ ቀላያት ተቀደዱ፥ ደመናትም ጠልን ያንጠባጥባሉ።
21ልጄ ሆይ፥ እነዚህ ከዓይኖችህ አይራቁ፤ መልካም ጥበብንና ጥንቃቄን ጠብቅ።
22ለነፍስህም ሕይወት ይሆናሉ፥ ለአንገትህም ሞገስ።
23የዚያን ጊዜ መንገድህን ተማምነህ ትሄዳለህ፥ እግርህም አይሰነካከልም።
24በተኛህ ጊዜ አትፈራም፤ ትተኛለህ፥ እንቅልፍህም የጣፈጠ ይሆንልሃል።
25ድንገት ከሚያስፈራ ነገር፥ ከሚመጣውም ከኃጥኣን ጥፋት አትፈራም፤
26እግዚአብሔር መታመኛህ ይሆናልና፥ እግርህም እንዳይጠመድ ይጠብቅሃልና።
27ለተቸገረው ሰው በጎ ነገርን ማድረግ አትከልክል፥ ልታደርግለት የሚቻልህ ሲሆን።
28ወዳጅህን። ሂድና ተመለስ፤ ነገ እሰጥሃለሁ አትበለው። በጎ ነገርን ማድረግ ሲቻልህ።
29በወዳጅህ ላይ ክፉ አትሥራ፥ እርሱ ተማምኖ ከአንተ ጋር ተቀምጦ ሳለ።
30ከሰው ጋር በከንቱ አትጣላ፥ እርሱ ክፉ ካልሠራብህ።
31በግፈኛ ሰው አትቅና፥ መንገዱንም ሁሉ አትምረጥ።
32ጠማማ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ርኩስ ነውና፤ ወዳጅነቱ ግን ከቅኖች ጋር ነው።
33የእግዚአብሔር መርገም በኃጥእ ቤት ነው፥ የጻድቃን ቤት ግን ይባረካል።
34በፌዘኞች እርሱ ያፌዛል፥ ለትሑታን ግን ሞገስን ይሰጣል።
35ጠቢባን ክብርን ይወርሳሉ፤ የሰነፎች ከፍታቸው ግን መዋረድ ነው።