ምዕራፍ 31
1እናቱ እርሱን ያስተማረችበት የማሣ ንጉሥ የልሙኤል ቃል።
2ልጄ ሆይ፥ ምንድር ነው? የሆዴ ልጅ ሆይ፥ ምንድር ነው? የስእለቴ ልጅ ሆይ፥ ምንድር ነው?
3ጕልበትህን ለሴቶች አትስጥ፥ መንገድህንም ነገሥታትን ለሚያጠፉ።
4ለነገሥታት አይገባም፥ ልሙኤል ሆይ፥ ነገሥታት የወይን ጠጅ ይጠጡ ዘንድ አይገባም። መሳፍንትም። ብርቱ መጠጥ ወዴት ነው? ይሉ ዘንድ፤
5እንዳይጠጡና ሕግን እንዳይረሱ፥ የድሀ ልጆችንም ፍርድ እንዳያጐድሉ።
6ለጥፋት ለቀረበው ሰው ብርቱ መጠጥ ስጡት፥ ነፍሱ ለመረረውም የወይን ጠጅ ስጡት፤
7ይጠጣ ድህነቱንም ይርሳ፥ ጕስቍልናውንም ከእንግዲህ ወዲህ አያስብ።
8አፍህን ስለ ዲዳው ክፈት፥ ተስፋ ስለሌላቸውም ሁሉ ተፋረድ።
9አፍህን ክፍት፥ በእውነትም ፍረድ፤ ለድሀና ለምስኪን ፍረድ።
10ልባም ሴትን ማን ሊያገኛት ይችላል? ዋጋዋ ከቀይ ዕንቍ እጅግ ይበልጣል።
11የባልዋ ልብ ይታመንባታል። ምርኮም አይጐድልበትም።
12ዕድሜዋን ሙሉ መልካም ታደርግለታለች፥ ክፉም አታደርግም።
13የበግ ጠጕርና የተልባ እግር ትፈልጋለች፥ በእጆችዋም ደስ ብሎአት ትሠራለች።
14እርስዋ እንደ ነጋዴ መርከብ ናት፤ ከሩቅ አገር ምግብዋን ትሰበስባለች።
15ገና ሌሊት ሳለ ትነሣለች ለቤትዋም ሰዎች ምግባቸውን፥ ለገረዶችዋም ተግባራቸውን ትሰጣለች።
16እርሻንም ተመልክታ ትገዛለች፤ ከእጅዋም ፍሬ ወይን ትተክላለች።
17ወገብዋን በኃይል ትታጠቃለች፥ ክንድዋንም ታበረታለች።
18ንግድዋ መልካም እንደ ሆነ ትመለከታለች፤ መብራትዋ በሌሊት አይጠፋም።
19እጅዋን ወደ አመልማሎ ትዘረጋለች፥ ጣቶችዋም እንዝርትን ይይዛሉ።
20እጅዋን ወደ ድሀ ትዘረጋለች፥ ወደ ችግረኛም እጅዋን ትሰድዳለች።
21ለቤትዋ ሰዎች ከበረዶ ብርድ የተነሣ አትፈራም፥ የቤትዋ ሰዎች ሁሉ እጥፍ ድርብ የለበሱ ናቸውና።
22ለራስዋም ግብረ መርፌ ስጋጃ ትሠራለች ጥሩ በፍታና ቀይ ግምጃ ትለብሳለች።
23ባልዋ በአገር ሽማግሌዎች መካከል በሸንጎ በተቀመጠ ጊዜ በበር የታወቀ ይሆናል።
24የበፍታ ቀሚስ እየሠራች ትሸጣለች፥ ለነጋዴም ድግ ትሸጣለች።
25ብርታትና ከበሬታ ልብስዋ ነው፤ በኋላም ዘመን ላይ ትስቃለች።
26አፍዋን በጥበብ ትከፍታለች፤ የርኅራኄም ሕግ በምላስዋ አለ።
27የቤትዋንም ሰዎች አካሄድ በደኅና ትመለከታለች፥ የሀኬትንም እንጀራ አትበላም።
28ልጆችዋ ይነሣሉ፥ ምስጋናዋንም ይናገራሉ፤ ባልዋ ደግሞ እንዲህ ብሎ ያመሰግናታል።
29መልካም ያደረጉ ብዙ ሴቶች አሉ፥ አንቺ ግን ከሁሉ ትበልጫለሽ።
30ውበት ሐሰት ነው፥ ደም ግባትም ከንቱ ነው፤ እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን እርስዋ ትመሰገናለች።
31ከእጅዋ ፍሬ ስጡአት፥ ሥራዎችዋም በሸንጎ ያመስግኑአት።