ምዕራፍ 7
1ልጄ ሆይ፥ ቃሌን ጠብቅ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽግ።
2ትእዛዜን ጠብቅ በሕይወትም ትኖራለህ፤ ሕጌንም እንደ ዓይንህ ብሌን ጠብቅ፤
3በጣቶችህ እሰራቸው፤ በልብህ ጽላት ጻፋቸው።
4ጥበብን። አንቺ እኅቴ ነሽ በላት፥ ማስተማውልንም። ወዳጄ ብለህ ጥራት፥
5ከጋለሞታ ሴት ትጠብቅህ ዘንድ ቃልዋን ካለዘበች ከሌላይቱ ሴት።
6በቤቴ መስኮት ሆኜ ወደ አደባባይ ተመለከትሁ፤
7ከአላዋቂዎች መካከል አስተዋልሁ፤ ከጐበዛዝትም መካከል ብላቴናውን አእምሮ ጐድሎት አየሁ፥
8በአደባባይ ሲሄድ በቤትዋም አቅራቢያ ሲያልፍ፤ የቤትዋን መንገድ ይዞ ወደ እርስዋ አቀና፥
9ማታ ሲመሽ፥ ውድቅትም ሲሆን፥ በሌሊትም በጽኑ ጨለማ።
10እነሆ፥ ሴት ተገናኘችው የጋለሞታ ልብስ የለበሰች፥ ነፍሳትን ለማጥመድ የተዘጋጀች።
11ሁከተኛና አባያ ናት፥ እግሮችዋም በቤትዋ አይቀመጡም፤
12አንድ ጊዜ በጎዳና፥ አንድ ጊዜ በአደባባይ፥ በማዕዘኑም ሁሉ ታደባለች።
13ያዘችውም ሳመችውም፤ ፊትዋም ያለ እፍረት ሆኖ እንዲህ አለችው።
14መሥዋዕትንና የደኅንነት ቍርባንን ማቅረብ ነበረብኝ፤ ዛሬ ስእለቴን ፈጸምሁ።
15ስለዚህ እንድገናኝህ፥ ፊትህንም በትጋት ለመሻት ወጥቻለሁ፥ አግኝቼሃለሁም።
16በአልጋዬ ላይ ማለፊያ ሰርፍ ዘርግቼበታለሁ፥ የግብጽንም ሽመልመሌ ለሀፍ።
17በመኝታዬ ከርቤንና ዓልሙን ቀረፋም ረጭቼበታለሁ።
18ና፥ እስኪነጋ ድረስ በፍቅር እንርካ፥ በተወደደ መተቃቀፍም ደስ ይበለን።
19ባለቤቴ በቤቱ የለምና፥ ወደ ሩቅ መንገድ ሄዶአልና፤
20በእጁም የብር ከረጢት ወስዶአል፤ ሙሉ ጨረቃ በሆነች ጊዜ ወደ ቤቱ ይመለሳል።
21በብዙ ጨዋታዋ እንዲስት ታደርገዋለች፤ በከንፈርዋ ልዝብነት ትጐትተዋለች።
22እርሱ እንዲህ ስቶ ይከተላታል፥ በሬ ለመታረድ እንዲነዳ፥ ውሻም ወደ እስራት እንዲሄድ፥
23ወፍ ወደ ወጥመድ እንደሚቸኩል፥ ለነፍሱ ጥፋት እንደሚሆን ሳያውቅ፥ ፍላጻ ጕበቱን እስኪሰነጥቀው ድረስ።
24ልጆቼ ሆይ፥ አሁን እንግዲህ ስሙኝ ወደ አፌም ቃል አድምጡኝ።
25ልብህ ወደ መንገድዋ አያዘንብል በጎዳናዋ አትሳት።
26ወግታ የጣለቻቸው ብዙ ናቸውና፤ እርስዋም የገደለቻቸው እጅግ ብዙ ናቸው።
27ቤትዋ የሲኦል መንገድ ነው፤ ወደ ሞት ማጀት የሚወርድ ነው።