ምዕራፍ 23
1የዳዊትም የመጨረሻ ቃሉ ይህ ነው። ከፍ ከፍ የተደረገው፥ በያዕቆብም አምላክ የተቀባው፥ በእስራኤል ዘንድ መልካም ባለ ቅኔ የሆነ፥ የእሴይ ልጅ የዳዊት ንግግር፤
2የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ተናገረ፤ ቃሉም በአንደበቴ ላይ ነበረ።
3የእስራኤል አምላክ ተናገረኝ፤ የእስራኤል ጠባቂ እንዲህ አለ። በሰው ላይ በጽድቅ የሚሠለጥን፥ በእግዚአብሔርም ፍርሃት የሚነግሥ፥
4እርሱ እንደ ማለዳ ብርሃን እንደ ፀሐይ አወጣጥ፥ በጥዋትም ያለ ደመና እንደሚደምቅ፥ ከዝናብ በኋላ ከምድር እንደሚበቅል ልምላሜ ይሆናል።
5በውኑ ቤቴ በእግዚአብሔር ዘንድ እንዲሁ አይደለምን? ከእኔም ጋር በሁሉ ነገር ቅንና ጽኑ የሆነውን የዘላለም ቃል ኪዳን አድርጎአል፤ መድኃኒቴንና ፈቃዴን ሁሉ ያበቅላል።
6ዓመፀኞች ሁሉ ግን ሰው በእጁ እንደማይዘው፥ እንደ ተጣለ እሾህ ናቸው።
7ማናቸውም ሰው ይነካው ዘንድ ቢወደድ፥ በእጁ ብረትና የጦሩን የቦ ይይዛል፤ በሥራቸውም በእሳት ፈጽሞ ይቃጠላሉ።
8የዳዊት ኃያላን ስም ይህ ነው። የአለቆች አለቃ የሆነ ከነዓናዊው ኢያቡስቴ ነበረ፤ እርሱም ጦሩን አንሥቶ ስምንት መቶ ያህል በአንድ ጊዜ ገደለ።
9ከእርሱም በኋላ የአሆሃዊው የዱዲ ልጅ ኤልያናን ነበረ፤ ለሰልፍ የተሰበሰቡትን ፍልስጥኤማውያንን በተገዳደሩ ጊዜ ከዳዊት ጋር ከሦስቱ ኃያላን አንዱ እርሱ ነበረ፤ የእስራኤልም ሰዎች ተመለሱ።
10እርሱ ግን ተነሥቶ እጁ እስኪደክምና ከሰይፉ ጋር እስኪጣበቅ ድረስ ፍልስጥኤማውያንን መታ፤ በዚያም ቀን እግዚአብሔር ታላቅ መድኃኒት አደረገ፤ ሕዝቡም ከእርሱ በኋላ ምርኮ ለመግፈፍ ብቻ ተመለሰ።
11ከእርሱም በኋላ የአሮዳዊው የአጌ ልጅ ሣማ ነበረ። ፍልስጥኤማውያንም ምስር በሞላበት እርሻ በአንድነት ሆነው ተከማችተው ነበር፤ ሕዝቡም ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ።
12እርሱ ግን በእርሻው መካከል ቆሞ ጠበቀ፥ ፍልስጥኤማውያንንም ገደለ፤ እግዚአብሔርም ታላቅ መድኃኒትአደረገ።
13ከሠላሳውም አለቆች ሦስቱ ወርደው በመከር ጊዜ ወደ ዳዊት ወደ ዓዶላም ዋሻ መጡ፤ የፍልስጥኤማውያንም ጭፍራ በራፋይም ሸለቆ ሰፍሮ ነበር።
14በዚያ ጊዜም ዳዊት በምሽጉ ውስጥ ነበረ፥ የፍልስጥኤማውያንም ጭፍራ በዚያ ጊዜ በቤተ ልሔም ነበረ።
15ዳዊትም። በበሩ አጠገብ ካለችው ከቤተ ልሔም ምንጭ ውኃ ማን ባጠጣኝ? ብሎ ተመኘ።
16ሦስቱም ኃያላን የፍልስጥኤማውያንን ሠራዊት ቀድደው ሄዱ፥ በበሩም አጠገብ ካለችው ከቤተ ልሔም ምንጭ ውኃ ቀዱ፥ ይዘውም ለዳዊት አመጡለት፤ እርሱ ግን ሊጠጣ አልወደደም፥ ነገር ግን ለእግዚአብሔር አፍስሶ።
17አቤቱ፥ ይህን አደርግ ዘንድ ከእኔ ይራቅ፤ በነፍሳቸው ደፍረው የሄዱ ሰዎች ደም አይደለምን? ብሎ ይጠጣ ዘንድ አልወደደም። ሦስቱ ኃያላን ያደረጉት ይህ ነው።
18የጽሩያም ልጅ የኢዮአብ ወንድም አቢሳ የሠላሳው አለቃ ነበረ። እርሱም ጦሩን በሦስቱ መቶ ላይ አንሥቶ ገደላቸው፤ ስሙም እንደ ሦስቱ ተጠርቶ ነበር።
19እርሱ በሠላሳው መካከል የከበረ አልነበረምን? ስለዚህ አለቃቸው ሆኖ ነበር፤ ነገር ግን ወደ ሦስቱ አልደረሰም።
20በቀብጽኤል የነበረው ታላቅ ሥራ ያደረገው የጽኑዕ ሰው የዮዳሄ ልጅ በናያስ የሞዓባዊውን የቀብስኤልን ሁለት ልጆች ገደለ፤ በአመዳዩም ወራት ወርዶ በጕድጓድ ውስጥ አንበሳ ገደለ።
21ረጅሙንም ግብጻዊ ሰው ገደለ፤ ግብጻዊው በእጁ ጦር ነበረው፤ በናያስ ግን በትር ይዞ ወደ እርሱ ወረደ፥ ከግብጻዊውም እጅ ጦሩን ነቅሎ በገዛ ጦሩ ገደለው።
22የዮዳሄ ልጅ በናያስ ያደረገው ይህ ነው፤ ስሙም እንደ ሦስቱ ኃያላን ተጠርቶ ነበር።
23ከሠላሳውም ይልቅ የከበረ ነበረ፥ ነገር ግን ወደ ሦስቱ አልደረሰም። ዳዊትም በክብር ዘበኞቹ ላይ ሾመው።
24የኢዮአብም ወንድም አሣሄል በሠላሳው መካከል ነበረ፥ የቤተ ልሔም ሰው የዱዲ
25ልጅ ኤልያናን፥ አሮዳዊው ሣማ፥ ሒሮዳዊው ኤሊቃ፥
26ፈልጣዊው ሴሌስ፥ የቴቁሐዊው
27የዒስካ ልጅ ዒራስ፥ ዓናቶታዊው
28አቢዔዜር፥ ኩሳታዊው ምቡናይ፥ አሆሃዊው
29ጸልሞን፥ ነጦፋዊው ኖኤሬ፥ የነጦፋዊው የበዓና ልጅ ሔሌብ፥ ከብንያም ወገን
30ከጊብዓ የሪባይ ልጅ ኢታይ፥ ጲርዓቶናዊው በናያስ፥ የገዓስ ወንዝ ሰው
31ሂዳይ፥ ዓረባዊው አቢዓልቦን፥ በርሑማዊው
32ዓዝሞት፥ ሸዓልቦናዊው ኤሊያሕባ፥
33የአሳን ልጆች፥ ዮናታን፥ አሮዳዊው ሣማ
34የአሮዳዊው የአራር ልጅ አምናን፥ የማዕካታዊው ልጅ የአሐስባይ ልጅ ኤሌፋላት፥ የጊሎናዊው የአኪጦፌል ልጅ ኤልያብ፥
35ቀርሜሎሳዊው ሐጽሮ፥ አርባዊው ፈዓራይ፥
36የሱባ ሰው የናታን ልጅ ይግዓል፥ ጋዳዊው
37ባኒ፥ የጽሩያ ልጅ የኢዮአብ ጋሻ ጃግሬዎች አሞናዊው ጼሌቅ፥ ብኤሮታዊው
38ነሃራይ፥ ይትራዊው ዒራስ፥ ይትራዊው
39ጋሬብ፥ ኬጢያዊው ኦርዮ፤ ሁሉ በሁሉ ሠላሳ ሰባት ናቸው።