English

ምዕራፍ 19

1አክዓብም ኤልያስ ይህን ሁሉ እንዳደረገ፥ ነቢያትንም ሁሉ በሰይፍ እንደ ገደለ ለኤልዛቤል ነገራት።
2ኤልዛቤልም። ነገ በዚህ ጊዜ ነፍስህን ከእነዚህ እንደ አንዲቱ ነፍስ ባላደርጋት፥ አማልክት ይህን ያድርጉብኝ ይህንም ይጨምሩብኝ ብላ ወደ ኤልያስ መልእክተኛ ላከች።
3ኤልያስም ፈርቶ ተነሣ፥ ነፍሱንም ሊያድን ሄደ፥ በይሁዳም ወዳለው ወደ ቤርሳቤህ መጥቶ ብላቴናውን በዚያ ተወ።
4እርሱም አንድ ቀን የሚያህል መንገድ በምድረ በዳ ሄደ፤ መጥቶም ከክትክታ ዛፍ በታች ተቀመጠና። ይበቃኛል፤ አሁንም፥ አቤቱ፥ እኔ ከአባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰድ ብሎ እንዲሞት ለመነ።
5በክትክታውም ዛፍ በታች ተጋደመ እንቅልፍም አንቀላፋ፤ እነሆም፥ መልአክ ዳሰሰውና። ተነሥተህ ብላ አለው።
6ሲመለከትም፥ እነሆ፥ በራሱ አጠገብ የተጋገረ እንጎቻና በማሰሮ ውኃ አገኘ። በላም ጠጣም፥ ተመልሶም ተኛ።
7የእግዚአብሔር መልአክ ደግሞ ሁለተኛ ጊዜ መጥቶ ዳሰሰውና። የምትሄድበት መንገድ ሩቅ ነውና ተነሥተህ ብላ አለው።
8ተነሥቶም በላ ጠጣም፤ በዚያም ምግብ ኃይል እስከ እግዚአብሔር ተራራ እስከ ኮሬብ ድረስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሄደ።
9እዚያም ወዳለ ዋሻ መጣ፥ በዚያም አደረ፤ እነሆም። ኤልያስ ሆይ፥ በዚህ ምን ታደርጋለህ? የሚል የእግዚአብሔር ቃል ወደ እርሱ መጣ።
10እርሱም። ለሠራዊት አምላክ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ፤ የእስራኤል ልጆች ቃል ኪዳንህን ትተዋልና፥ መሠዊያዎችህንም አፍርሰዋልና፥ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋልና፤ እኔም ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ ነፍሴንም ሊወስዱአት ይሻሉ አለ።
11እርሱም። ውጣ፥ በተራራውም ላይ በእግዚአብሔር ፊት ቁም አለ። እነሆም፥ እግዚአብሔር አለፈ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ትልቅና ብርቱ ነፋስ ተራሮቹን ሰነጠቀ ዓለቶቹንም ሰባበረ፥ እግዚአብሔር ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም። ከነፋሱም በኋላ የምድር መናወጥ ሆነ፥ እግዚአብሔር ግን በምድር መናወጥ ውስጥ አልነበረም።
12ከምድር መናወጥ በኋላ እሳት ሆነ፥ እግዚአብሔር ግን በእሳቱ ውስጥ አልነበረም። ከእሳቱም በኋላ ትንሽ የዝምታ ድምፅ ሆነ።
13ኤልያስም ያን በሰማ ጊዜ ፊቱን በመጐናጸፊያው ሸፈነ፥ ወጥቶም በዋሻው ደጃፍ ቆመ። እነሆ። ኤልያስ ሆይ፥ በዚህ ምን ታደርጋለህ? የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ።
14እርሱም። ለሠራዊት አምላክ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ፤ የእስራኤል ልጆች ቃል ኪዳንህን ትተዋልና፥ መሠዊያዎችህንም አፍርሰዋልና፥ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋልና፤ እኔም ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ ነፍሴንም ሊወስዱአት ይሻሉ አለ።
15እግዚአብሔርም አለው። ሂድ፥ በመጣህበትም መንገድ በምድረ በዳ ወደ ደማስቆ ተመለስ፤ ከዚያም በደረስህ ጊዜ በሶርያ ላይ ንጉሥ ይሆን ዘንድ አዛሄልን ቅባው፤
16በእስራኤልም ላይ ንጉሥ ይሆን ዘንድ የናሜሲን ልጅ ኢዩን ቅባው፤ በፋንታህም ነቢይ ይሆን ዘንድ የአቤልምሖላን ሰው የሣፋጥን ልጅ ኤልሳዕን ቅባው ከአዛሄልም ሰይፍ ያመለጠውን ሁሉ።
17ኢዩ ይገድለዋል፤ ከኢዩም ሰይፍ ያመለጠውን ሁሉ ኤልሳዕ ይገድለዋል።
18እኔም ከእስራኤል ጕልበታቸውን ለበኣል ያላንበረከኩትን ሁሉ፥ በአፋቸውም ያልሳሙትን ሁሉ፥ ሰባት ሺህ ሰዎች ለእኔ አስቀራለሁ።
19ከዚያም ሄደ፥ የሣፋጥንም ልጅ ኤልሳዕን በአሥራ ሁለት ጥማድ በሬዎች ሲያርስ፥ እርሱም ከአሥራ ሁለተኛው ጋር ሆኖ አገኘው። ኤልያስም ወደ እርሱ አልፎ መጐናጸፊያውን ጣለበት።
20በሬዎቹንም ተወ፥ ከኤልያስም በኋላ ሮጦ። አባቴንና እናቴን እስማቸው ዘንድ፥ እባክህ፥ ተወኝ፥ ከዚያም በኋላ እከተልሃለሁ አለው። እርሱም። ሂድና ተመለስ፤ ምን አድርጌልሃለሁ? አለው።
21ከእርሱም ዘንድ ተመልሶ ሁለቱን በሬዎች ወስዶ አረዳቸው፥ ሥጋቸውንም በበሬዎቹ ዕቃ ቀቀለው፥ ለሕዝቡም ሰጣቸው፥ በሉም፤ እርሱም ተነሥቶ ኤልያስን ተከትሎ ሄደ፥ ያገለግለውም ነበር።