ምዕራፍ 9
1ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቤት፥ የንጉሡን ቤትና ሰሎሞን የወደደውን የልቡን አሳብ ሁሉ ሠርቶ በፈጸመ ጊዜ፥
2እግዚአብሔር በገባዖን ለሰሎሞን እንደ ተገለጠለት ዳግመኛ ተገለጠለት።
3እግዚአብሔርም አለው። በፊቴ የጸለይኸውን ጸሎትህንና ልመናህን ሰምቻለሁ፤ ለዘላለምም ስሜ በዚያ ያድር ዘንድ ይህን የሠራኸውን ቤት ቀድሻለሁ፤ ዓይኖቼና ልቤም በዘመኑ ሁሉ በዚያ ይሆናሉ።
4ዳዊትም አባትህ በየዋህ ልብና በቅንነት እንደ ሄደ አንተ ደግሞ በፊቴ ብትሄድ፥ ያዘዝሁህንም ሁሉ ብታደርግ፥ ሥርዓቴንም ፍርዴንም ብትጠብቅ፥
5እኔ። ከእስራኤል ዙፋን ከዘርህ ሰው አታጣም ብዬ ለአባትህ ለዳዊት እንደ ተናገርሁ፥ የመንግሥትህን ዙፋን በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጸናለሁ።
6እናንተና ልጆቻችሁ ግን እኔን ከመከትል ብትመለሱ፥ የሰጠኋችሁንም ትእዛዜንና ሥርዓቴን ባትጠብቁ፥ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ብታመልኩ፥ ብትሰግዱላቸውም፥
7እስራኤልን ከሰጠኋቸው ምድር አጠፋቸዋለሁ፤ ለስሜም የቀደስሁትን ይህን ቤት ከፊቴ እጥለዋለሁ፤ እስራኤልም በአሕዛብ ሁሉ መካከል ምሳሌና ተረት ይሆናሉ።
8ከፍ ከፍ ብሎ የነበረውም ይህ ቤት ባድማ ይሆናል፤ በዚያም የሚያልፍ ሁሉ እያፍዋጨ። እግዚአብሔር በዚህ አገርና በዚህ ቤት ስለምን እንዲህ አደረገ? ብሎ ይደነቃል።
9መልሰውም። ከግብጽ ምድር አባቶቻቸውን ያወጣውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን ትተው ሌሎችንም አማልክት ስለ ተከተሉ፥ ስለ ሰገዱላቸውም፥ ስለ አመለኩአቸውም፥ ስለዚህ እግዚአብሔር ይህን ክፉ ነገር ሁሉ አመጣባቸው ይላሉ።
10ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቤትና የንጉሡን ቤት ሁለቱን ቤቶች የሠራበት ሀያ ዓመት በተፈጸመ ጊዜ፥
11ንጉሡ ሰሎሞን በገሊላ ምድር ያሉትን ሀያ ከተሞች ለኪራም ሰጠው። የጢሮስም ንጉሥ ኪራም የሚሻውን ያህል የዝግባና የጥድ እንጨት የሚሻውንም ያህል ወርቅ ሁሉ ለሰሎሞን ሰጥቶት ነበር።
12ኪራምም ሰሎሞን የሰጠውን ከተሞች ያይ ዘንድ ከጢሮስ ወጣ፤ ደስም አላሰኙትም።
13እርሱም። ወንድሜ ሆይ፥ የሰጠኸኝ እነዚህ ከተሞች ምንድር ናቸው? አለ። እስከ ዛሬም ድረስ የከቡል አገር ተብለው ተጠሩ።
14ኪራምም መቶ ሀያ መክሊት ወርቅ ለንጉሡ ላከ።
15ንጉሡም ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤትና የራሱን ቤት፥ ሚሎንም፥ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር፥ ሐጾርንም፥ መጊዶንም፥ ጌዝርንም ይሠራ ዘንድ ገባሮችን መልምሎ ነበር።
16የግብጽም ንጉሥ ፈርዖን ወጥቶ ጌዝርን ይዞ ነበር፥ በእሳትም አቃጥሎ ነበር፥ በከተማም የኖሩትን ከነዓናውያን ገድሎ ነበር፤ ለልጁም ለሰሎምን ሚስት ትሎት አድርጎ ሰጥቶአት ነበር።
17ሰሎሞንም ጌዝርን፥ የታችኛውንም ቤት
18ሖሮን፥ ባዕላትንም፥ በምድረ በዳም አገር ያለችውን ተድሞርን፥
19ለሰሎሞንም የነበሩትን የዕቃ ቤት ከተሞች ሁሉ፥ የሰረገላውንም ከተሞች፥ የፈረሰኞችንም ከተሞች፥ በኢየሩሳሌምም በሊባኖስም በመንግሥቱም ምድር ሁሉ ሰሎሞን ይሠራ ዘንድ የወደደውን ሁሉ ሠራ።
20ከእስራኤልም ልጆች ዘንድ ያልነበሩትን ከአሞራውያንና ከኬጢያውያን፥ ከፌርዛውያን፥ ከኤዊያውያንና ከኢያቡሳውያን የቀሩትን፥
21የእስራኤልም ልጆች ያጠፉአቸው ዘንድ ያልቻሉትን፥ በኋላቸው የቀሩትን ልጆቻቸውን፥ ሰሎሞን እስከ ዛሬ ድረስ ገባሮች አድርጎ መለመላቸው።
22ሰሎሞንም ከእስራኤል ልጆች ማንንም ባሪያ አላደረገም፤ እነርሱ ግን ሰልፈኞች፥ ሎሌዎችም፥ መሳፍንትም፥ አለቆችም፥ የሰረገሎችና የፈረሶች ባልደራሶች ነበሩ።
23ሰሎሞንም በሚሠራው ሥራ ላይ ሠራተኛውን ሕዝብ የሚያዝዙ አለቆች አምስት መቶ አምሳ ነበሩ።
24የፈርዖንም ልጅ ከዳዊት ከተማ ሰሎሞን ወደ ሠራላት ወደ ቤትዋ ወጣች በዚያን ጊዜም ሚሎን ሠራ።
25ሰሎሞንም በየዓመቱ ሦስት ጊዜ የሚቃጠለውንና የደኅንነቱን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በሠራው መሠዊያ ላይ ያሳርግ ነበር፤ በእግዚአብሔር ፊት ባለው መሠዊያ ላይ ዕጣን ያሳርግ ነበር፤ ቤቱንም ጨረሰ።
26ንጉሡም ሰሎሞን በኤዶምያስ ምድር በኤርትራ ባሕር ዳር በኤሎት አጠገብ ባለችው በዔጽዮንጋብር መርከቦችን ሠራ።
27ኪራምም በእነዚያ መርከቦች ከሰሎሞን ባሪያዎች ጋር የባሕሩን ነገር የሚያውቁ መርከበኞች ባሪያዎቹን ሰደደ።
28ወደ ኦፊርም መጡ፥ ከዚያም አራት መቶ ሀያ መክሊተ ወርቅ ወሰዱ፥ ወደ ንጉሡም ወደ ሰሎሞን ይዘው መጡ።