English

ምዕራፍ 10

1ለአክዓብም በሰማርያ ሰባ ልጆች ነበሩት፤ ኢዩም ደብዳቤ ጻፈ፤ የአክዓብን ልጆች ለሚያሳድጉ ለሰማርያ ታላላቆችና ሽማግሌዎች።
2ይህ ደብዳቤ አሁን በደረሳችሁ ጊዜ የጌታችሁ ልጆች ሰረገሎችና ፈረሶችም የተመሸገችም ከተማ መሣሪያዎችም በእናንተ ዘንድ አሉና፥
3ከጌታችሁ ልጆች ደስ የሚያሰኛችሁንና የሚሻላችሁን ምረጡ፥ በአባቱም ዙፋን አስቀምጡት፥ ስለ ጌታችሁም ቤት ተዋጉ ብሎ ወደ ሰማርያ ሰደደ፤
4እነርሱ ግን እጅግ ፈርተው። እነሆ፥ ሁለቱ ነገሥታት በፊቱ ይቆሙ ዘንድ አልቻሉም፤ እኛስ እንዴት እንቆማለን? አሉ።
5የቤቱ አለቃ፥ የከተማይቱም አለቃ፥ ሽማግሌዎችና ልጆቹን የሚያሳድጉ። እኛ ባሪያዎችህ ነን፥ ያዘዝኸንም ሁሉ እናደርጋለን፤ ንጉሥም በላያችን አናነግሥም፤ የምትወድደውን አድርግ ብለው ወደ ኢዩ ላኩ።
6ሁለተኛም። ወገኖቼስ እንደ ሆናችሁ፥ ነገሬንም ከሰማችሁ፥ የጌታችሁን ልጆች ራስ ቍረጡ፥ ነገም በዚህ ሰዓት ወደ ኢይዝራኤል ወደ እኔ ይዛችሁ ኑ ብሎ ደብዳቤ ጻፈላቸው። የንጉሡም ልጆች ሰባው ሰዎች በሚያሳድጓቸው በከተማይቱ ታላላቆች ዘንድ ነበሩ።
7ደብዳቤውም በደረሳቸው ጊዜ የንጉሡን ልጆች ሰባውን ሰዎች ይዘው ገደሉአቸው፤ ራሳቸውንም በቅርጫት አድርገው ወደ እርሱ ወደ ኢይዝራኤል ላኩ።
8መልእክተኛም መጥቶ። የንጉሡን ልጆች ራስ ይዘው መጥተዋል ብሎ ነገረው። እርሱም። እስከ ነገ ድረስ በበሩ አደባባይ ሁለት ክምር አድርጋችሁ አኑሩአቸው አለ።
9በነጋውም ወጥቶ ቆመ፥ ሕዝቡንም ሁሉ። እናንተ ንጹሐን ናችሁ፤ እነሆ፥ ጌታዬን የወነጀልሁ የገደልሁትም እኔ ነኝ፤ እነዚህንስ ሁሉ የገደለ ማን ነው?
10እግዚአብሔር በአክዓብ ቤት ላይ ከተናገረው ከእግዚአብሔር ቃል በምድር ላይ አንዳች እንዳይወድቅ አሁን እወቁ፤ እግዚአብሔር በባሪያው በኤልያስ የተናገረውን አድርጎአል አላቸው።
11ኢዩም ከአክዓብ ቤት የቀረውን ሁሉ፥ ታላላቆቹንም ሁሉ፥ ወዳጆቹንና ካህናቱን ማንም ሳይቀር በኢይዝራኤል ገደላቸው።
12ተነሥቶም ወደ ሰማርያ ሄደ፤ በመንገድም ወዳለው ወደ በግ ጠባቂዎች ቤት በደረሰ ጊዜ፥
13ኢዩ ከይሁዳ ንጉሥ ከአካዝያስ ወንድሞች ጋር ተገናኝቶ። እናንተ እነማን ናችሁ? አለ። እነርሱም። እኛ የአካዝያስ ወንድሞች ነን፤ የንጉሡንና የእቴጌይቱን ልጆች ደኅንነት ለመጠየቅ እንወርዳለን አሉት።
14እርሱም። በሕይወታቸው ያዙአቸው አለ። ያዙአቸውም፥ በበግ ጠባቂዎችም ቤት አጠገብ ባለው ጕድጓድ አርባ ሁለቱን ሰዎች ገደሉአቸው፤ ማንንም አላስቀረም።
15ከዚያም በሄደ ጊዜ የሬካብን ልጅ ኢዮናዳብን ተገናኘው፤ ደኅንነቱንም ጠይቆ። ልቤ ከልብህ ጋር እንደ ሆነ ያህል ልብህ ከልቤ ጋር በቅንነት ነውን? አለው፤ ኢዮናዳብም። እንዲሁ ነው አለው። ኢዩም። እንዲሁ እንደ ሆነስ እጅህን ስጠኝ አለ። እጁንም ሰጠው፤ ወደ ሰረገላውም አውጥቶ ከእርሱ ጋር አስቀመጠውና።
16ከእኔ ጋር ና፥ ለእግዚአብሔርም መቅናቴን እይ አለው። በሰረገላውም አስቀመጠው።
17ወደ ሰማሪያም በመጣ ጊዜ ለኤልያስ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል እስኪያጠፋው ድረስ ከአክዓብ በሰማርያ የቀረውን ሁሉ ገደለ።
18ኢዩም ሕዝቡን ሁሉ ሰብስቦ። አክዓብ በኣልን በጥቂቱ አመለከው፤ ኢዩ ግን በብዙ ያመልከዋል።
19አሁንም የባኣልን ነቢያት ሁሉ፥ አገልጋዮቹንም ሁሉ፥ ካህናቱንም ሁሉ ወደ እኔ ጥሩ፤ ማንም አይቅር፤ ለባኣል ታላቅ መሥዋዕት አቀርባለሁ፥ የቀረውም ሁሉ በሕይወት አይኖርም አላቸው። ኢዩም የበኣልን አገልጋዮች ያጠፋ ዘንድ በተንኰል ይህን አደረገ።
20ኢዩም። ለበኣል ዋና ጉባኤ ቀድሱ አለ።
21እነርሱም አወጁ። ኢዩም ወደ እስራኤል ሁሉ ላከ፥ የበኣልም አገልጋዮች ሁሉ መጡ፤ ሳይመጣ የቀረ አንድ ስንኳ አልነበረም። ወደ በኣልም ቤት ገቡ፥ የበኣልም ቤት ከዳር እስከ ዳር ድረስ ሞልቶ ነበር፤
22ዕቃ ቤቱንም። ለበኣል አገልጋዮች ሁሉ ልብስ አውጣ አለው።
23ልብሱንም አወጣላቸው። ኢዩም የሬካብም ልጅ ኢዮናዳብ ወደ በኣል ቤት ገቡ። የበኣልንም አገልጋዮች። መርምሩ፥ ከበኣል አገልጋዮች ብቻ በቀር እግዚአብሔርን ከሚያመልኩ ወገን በእናንተ ዘንድ አንድ እንኳ እንዳይኖር ተመልከቱ አላቸው።
24የሚቃጠል መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕትም ያቀረቡ ዘንድ ገቡ፤ ኢዩም። በእጃችሁ አሳልፌ ከምሰጣችሁ ሰዎች አንድ ሰው ያመለጠ እንደ ሆነ ነፍሱ በዚያ ነፍስ ፋንታ ትሆናለች ብሎ በውጪ ሰማንያ ሰዎችን አዘጋጅቶ ነበር።
25የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አቅርበው በፈጸሙ ጊዜ ኢዩ ዘበኞቹንና አለቆቹን። ግቡና ግደሉአቸው፤ አንድም አይውጣ አላቸው። በሰይፍም ስለት ገደሉአቸው፤ ዘበኞችና አለቆችም ወደ ውጭ ጣሉአቸው፥ ወደ በኣልም ቤት ከተማ ሄዱ።
26ከበኣልም ቤት ሐውልቶቹን አወጡ አቃጠሉአቸውም።
27የበኣልን ሐውልት ቀጠቀጡ፥ የበኣልንም ቤት አፈረሱ፥ እስከ ዛሬም ድረስ የውዳቂ መጣያ አደረጉት።
28እንዲሁም ኢዩ በኣልን ከእስራኤል አጠፋ።
29ነገር ግን እስራኤልን ካሳተው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኃጢአት፥ በቤቴልና በዳን ከነበሩት ከወርቁ እምቦሶች፥ ኢዩ አልራቀም።
30እግዚአብሔርም ኢዩን። በፊቴ ቅን ነገር አድርገሃልና፥ በልቤም ያለውን ሁሉ በአክዓብ ቤት ላይ አድርገሃልና ልጆችህ እስከ አራት ትውልድ ድረስ በእስራኤል ዙፋን ላይ ይቀመጣሉ አለው።
31ኢዩ ግን በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ሕግ በፍጹም ልቡ ይሄድ ዘንድ አልተጠነቀቀም፤ እስራኤልንም ካሳተው ከኢዮርብዓም ኃጢአት አልራቀም።
32በዚያም ወራት እግዚአብሔር እስራኤልን ይከፋፍላቸው ዘንድ ጀመረ፤ አዛሄልም በእስራኤል ዳርቻ ሁሉ መታቸው።
33በዮርዳኖስ ምሥራቅ ያለውን የገለዓድን አገር ሁሉ፥ በአርኖን ወንዝ አጠገብ ካለችው ከአሮዔር ጀምሮ የጋድንና የሮቤልን የምናሴንም አገር፥ ገለዓድንና ባሳንን መታ።
34የቀረውም የኢዩ ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ ጭከናውም ሁሉ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
35ኢዩም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በሰማርያም ቀበሩት። በፋንታውም ልጁ ኢዮአካዝ ነገሠ።
36ኢዩም በሰማርያ በእስራኤል ላይ የነገሠበት ዘመን ሀያ ስምንት ዓመት ነበረ።