English

ምዕራፍ 17

1በይሁዳ ንጉሥ በአካዝ በአሥራ ሁለተኛው ዓመት የኤላ ልጅ ሆሴዕ በእስራኤል ላይ በሰማርያ ንጉሥ ሆነ፤ ዘጠኝ ዓመትም ነገሠ።
2በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ ነገር ግን ከእርሱ አስቀድሞ እንደ ነበሩት እንደ እስራኤል ነገሥታት አይደለም።
3የአሦርም ንጉሥ ስልምናሶር በእርሱ ላይ ወጣ፤ ሆሴዕም ተገዛለት፥ ግብርም አመጣለት።
4የአሦርም ንጉሥ በሆሴዕ ላይ ዓመፅ አገኘ፤ መልእክተኞችን ወደ ግብጽ ንጉሥ ወደ ሴጎር ልኮ ነበርና፤ እንደ ልማዱም በየዓመቱ ለአሦር ንጉሥ ግብር አልሰጠምና፤ ስለዚህ የአሦር ንጉሥ ይዞ በወህኒ ቤት አሰረው።
5የአሦርም ንጉሥ በምድር ሁሉ ላይ ወጣ፥ ወደ ሰማርያም ወጥቶ ሦስት ዓመት ከበባት።
6በሆሴዕ በዘጠኝኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ ሰማርያን ወሰደ፥ እስራኤልንም ወደ አሦር አፈለሰ፥ በአላሔና በአቦር በጎዛንም ወንዝ በሜዶንም ከተሞች አኖራቸው።
7የእስራኤልም ልጆች ከግብጽ ንጉሥ ከፈርዖን እጅ፥ ከግብጽ ምድር ያወጣቸውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን በድለው ነበርና፥ ሌሎችንም አማልክት አምልከው ነበርና፥
8እግዚአብሔርም ከእስራኤል ልጆች ፊት ባሳደዳቸው በአሕዛብ ሥርዓት፥ የእስራኤልም ነገሥታት ባደረጓት ሥርዓት ሄደው ነበርና እንደዚህ ሆነ።
9የእስራኤልም ልጆች በአምላካቸው በእግዚአብሔር ላይ ቅን ያልሆነን ንገር በስውር አደረጉ፤ በከተሞቻቸውም ሁሉ ከዘበኞች ግንብ ጀምሮ እስከ ተመሸገች ከተማ ድረስ በከፍታዎቹ ላይ መስገጃዎችን ሠሩ።
10በረጃጅሙ ኮረብታ ሁሉ ላይ በለመለመውም ዛፍ ሁሉ ታች ሐውልቶችንና የማምለኪያ ዐፀዶችን ተከሉ፤
11እግዚአብሔርም ከፊታቸው ያወጣቸው አሕዛብ እንዳደረጉት፥ በኮረብቶቹ መስገጃዎች ሁሉ ላይ ያጥኑ ነበር፤ እግዚአብሔርንም ያስቈጡ ዘንድ ክፉ ነገር አደረጉ፤
12እግዚአብሔርም የከለከላቸውን ጣዖቶች አመለኩ።
13እግዚአብሔርም። ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ለአባቶቻችሁም እንዳዘዝሁት፥ ባባሪያዎቼ በነቢያት የላክሁላችሁን ትእዛዜንና ሥርዓቴን ሕጌንም ሁሉ ጠብቁ ብሎ በነቢዩ ሁሉና በባለ ራእዩ አፍ ሁሉ በእስራኤልና በይሁዳ መሰከረ።
14ነገር ግን አምላካቸውን እግዚአብሔርን እንዳላመኑ እንደ አባቶቻቸው አንገት አንገታቸውን አደነደኑ እንጂ አልሰሙም።
15ሥርዓቱንም ከአባቶቻቸውም ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን፥ ያጸናላቸውንም ምስክሩን ናቁ፤ ከንቱ ነገርንም ተከተሉ፥ ምናምንቴዎችም ሆኑ፥ እግዚአብሔርም እንደ እነርሱ እንዳይሠሩ ያዘዛቸውን በዙሪያቸው ያሉትን አሕዛብን ተከተሉ።
16የአምላካቸውንም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ሁሉ ተዉ፥ ቀልጠው የተሠሩትንም የሁለቱን እንቦሶች ምስሎች አደረጉ፥ የማምለኪያ ዐፀድንም ተከሉ፥ ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ ሰገዱ፥ በኣልንም አመለኩ።
17ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በእሳት አሳለፉአቸው፥ ምዋርተኞችና አስማተኞችም ሆኑ፥ ያስቈጡትም ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር ለማድረግ ራሳቸውን ሸጡ።
18ስለዚህም እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ እጅግ ተቈጣ፥ ከፊቱም ጣላቸው፤ ከይሁዳም ነገድ ብቻ በቀር ማንም አልቀረም።
19ይሁዳም ደግሞ እስራኤል ባደረጋት ሥርዓት ሄደ እንጂ የአምላኩን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ አልጠበቀም።
20እግዚአብሔርም የእስራኤልን ዘር ሁሉ ጠላ፥ አስጨነቃቸውም፥ ከፊቱም እስኪጥላቸው ድረስ በበዝባዦች እጅ አሳልፎ ሰጣቸው።
21እስራኤልንም ከዳዊት ቤት ለየ፤ የናባጥንም ልጅ ኢዮርብዓምን አነገሡ፤ ኢዮርብዓምም እግዚአብሔርን ከመከተል እስራኤልን መለሰ፥ ታላቅም ኃጢአት አሠራቸው።
22የእስራኤልም ልጆች ኢዮርብዓም ባደረገው ኃጢአት ሁሉ ሄዱ፤
23እግዚአብሔርም በባሪያዎቹ በነቢያቱ ሁሉ አፍ እንደ ተናገረው እስራኤልን ከፊቱ እስኪያወጣ ድረስ ከእርስዋ አልራቁም። እስራኤልም እስከ ዛሬ ድረስ ከምድሩ ወደ አሦር ፈለሰ።
24የአሦርም ንጉሥ ከባቢሎንና ከኩታ ከአዋና ከሐማት ከሴፈርዋይም ሰዎችን አመጣ፥ በእስራኤልም ልጆች ፋንታ በሰማርያ ከተሞች አኖራቸው፤ ሰማርያንም ወረሱአት፤ በከተሞችዋም ተቀመጡ።
25በዚያም መቀመጥ በጀመሩ ጊዜ እግዚአብሔርን አይፈሩትም ነበር፤ እግዚአብሔርም አንበሶች ሰደደባቸው፥ ይገድሉአቸውም ነበር።
26ስለዚህም ለአሦር ንጉሥ። ያፈለስኻቸው፥ በሰማርያም ከተሞች ያኖርኻቸው የአገሩን አምላክ ወግ አላወቁም፤ የአገሩን አምላክ ወግ አላወቁምና አንበሶችን ሰድዶባቸዋል፥ እነሆም፥ ገደሉአቸው ብለው ተናገሩት።
27የአሦርም ንጉሥ። ከዚያ ካመጣችኋቸው ካህናት አንዱን ውሰዱ፤ ሄዶም በዚያ ይቀመጥ፥ የአገሩንም አምላክ ወግ ያስተምራቸው ብሎ አዘዘ።
28ከሰማርያም ካፈለሱአቸው ካህናት አንዱ መጥቶ በቤቴል ተቀመጠ፥ እግዚአብሔርንም እንዴት እንዲፈሩት ያስተምራቸው ነበር።
29በየሕዝባቸውም አምላካቸውን አደረጉ፥ ሰምራውያንም በሠሩት በኮረብታው መስገጃዎች ሕዝቡ ሁሉ በሚኖሩበት ከተሞቻቸው አኖሩአቸው።
30የባቢሎንም ሰዎች ሱኮትበኖትን ሠሩ፤ የኩታም ሰዎች ኤርጌልን ሠሩ፤
31የሐማትም ሰዎች አሲማትን ሠሩ፤ አዋውያንም ኤልባዝርንና ተርታቅን ሠሩ፤ የሴፈርዋይም ሰዎችም ለሴፈርዋይም አማልክት ለአድራሜሌክና ለአነሜሌክ ልጆቻቸውን በእሳት ያቃጥሉ ነበር።
32እግዚአብሔርንም ይፈሩ ነበር፥ ከመካከላቸውም ለኮረብታው መስገጃዎች ካህናት አደረጉ፥ በኮረብታውም መስገጃዎች ይሠዉ ነበር።
33እግዚአብሔርንም ሲፈሩ ከመካከላቸው እንደ ፈለሱት እንደ አሕዛብ ልማድ አምላካቸውን ያመልኩ ነበር።
34እስከ ዛሬ ድረስ እንደ ቀደመው ልማድ ያደርጋሉ፤ እግዚአብሔርንም አይፈሩም፥ እግዚአብሔርም እስራኤል ብሎ የጠራውን የያዕቆብን ልጆች እንዳዘዛቸው ሥርዓትና ፍርድ ሕግና ትእዛዝም አያደርጉም።
35እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፥ እንዲህም ብሎ አዘዛቸው። ሌሎችን አማልክት አትፍሩ፥ አትስገዱላቸው፥ አታምልኩአቸው፥ አትሠዉላቸው፤
36ነገር ግን በታላቅ ኃይል በተዘረጋችም ክንድ ከግብጽ ምድር ያወጣችሁን እግዚአብሔር እርሱን ፍሩ፥ ለእርሱም ስገዱ፥ ለእርሱም ሠዉ፤
37የጻፈላችሁንም ሥርዓትና ፍርድ ሕግና ትእዛዝም ለዘላለም ታደርጉ ዘንድ ጠብቁ፤ ሌሎችንም አማልክት አትፍሩ።
38ከእናንተም ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳን አትርሱ፤ ሌሎችንም አማልክት አትፍሩ።
39አምላካችሁን እግዚአብሔርን ፍሩ፤ እርሱም ከጠላቶቻችሁ ሁሉ እጅ ያድናችኋል።
40ነገር ግን እንደ ቀደመው ልማዳቸው አደረጉ እንጂ አልሰሙም።
41እነዚህም አሕዛብ እግዚአብሔርን ይፈሩ ነበር፤ ደግሞም የተቀረጹ ምስሎቻቸውን ያመልኩ ነበር፤ ልጆቻቸውም የልጅ ልጆቻቸውም አባቶቻቸው እንዳደረጉ እንዲሁ እስከ ዛሬ ድረስ ያደርጋሉ።