English

ምዕራፍ 5

1የሶርያ ንጉሥ ሠራዊት አለቃ ንዕማንም እግዚአብሔር በእርሱ እጅ ለሶርያ ደኅንነትን ስለ ሰጠ በጌታው ዘንድ ታላቅ ክቡር ሰው ነበረ፤ ደግሞም ጽኑዕ ኃያል ነበረ፥ ነገር ግን ለምጻም ነበረ።
2ከሶርያውያንም አገር አደጋ ጣዮች ወጥተው ነበር፥ ከእስራኤልም ምድር ታናሽ ብላቴና ሴት ማርከው ነበር፤ የንዕማንንም ሚስት ታገለግል ነበር።
3እመቤትዋንም። ጌታዬ በሰማርያ ካለው ከነቢዩ ፊት ቢደርስ ኖሮ ከለምጹ በፈወሰው ነበር አለቻት።
4ንዕማንም ገብቶ ለጌታው። ከእስራኤል አገር የሆነች አንዲት ብላቴና እንዲህና እንዲህ ብላለች ብሎ ነገረው።
5የሶርያም ንጉሥ ንዕማንን። ሂድ፥ ለእስራኤል ንጉሥ ደብዳቤ እልካለሁ አለው። እርሱም ሄደ፥ አሥርም መክሊት ብር፥ ስድስት ሺህም ወርቅ፥ አሥርም መለውጫ ልብስ በእጁ ወሰደ።
6ለእስራኤልም ንጉሥ። ይህች ደብዳቤ ወደ አንተ ስትደርስ ባሪያዬን ንዕማንን ከለምጹ ትፈውሰው ዘንድ እንደ ሰደድሁልህ እወቅ የሚል ደብዳቤ ወሰደ።
7የእስራኤልም ንጉሥ ደብዳቤውን ባነበበ ጊዜ ልብሱን ቀድዶ። ሰውን ከለምጹ እፈውስ ዘንድ ይህ ሰው ወደ እኔ መስደዱ እኔ በውኑ ለመግደልና ለማዳን የምችል አምላክ ሆኜ ነውን? ተመልከቱ፥ የጠብ ምክንያትም እንደሚፈልግብኝ እዩ አለ።
8የእግዚአብሔርም ሰው ኤልሳዕ የእስራኤል ንጉሥ ልብሱን እንደ ቀደደ በሰማ ጊዜ። ልብስህን ለምን ቀደድህ? ወደ እኔ ይምጣ፥ በእስራኤልም ዘንድ ነቢይ እንዳለ ያውቃል ብሎ ወደ ንጉሡ ላከ።
9ንዕማንም በፈረሱና በሰረገላው መጣ፥ በኤልሳዕም ቤት ደጃፍ ውጭ ቆመ።
10ኤልሳዕም። ሂድ፥ በዮርዳኖስም ሰባት ጊዜ ታጠብ፤ ሥጋህም ይፈወሳል፥ አንተም ንጹሕ ትሆናለህ ብሎ ወደ እርሱ መልእክተኛ ላከ።
11ንዕማን ግን ተቈጥቶ ሄደ፥ እንዲህም አለ። እነሆ፥ ወደ እኔ የሚመጣ፥ ቆሞም የአምላኩን የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ፥ የለምጹንም ስፍራ በእጁ ዳስሶ የሚፈውሰኝ መስሎኝ ነበር።
12የደማስቆ ወንዞች አባናና ፋርፋ ከእስራኤል ውኆች ሁሉ አይሻሉምን? በእነርሱስ ውስጥ መታጠብና መንጻት አይቻለኝም ኖሮአልን? ዘወርም ብሎ ተቈጥቶ ሄደ።
13ባሪያዎቹም ቀርበው። አባት ሆይ፥ ነቢዩ ታላቅ ነገርስ እንኳ ቢነግርህ ኖሮ ባደረግኸው ነበር፤ ይልቁንስ። ታጠብና ንጹሕ ሁን ቢልህ እንዴት ነዋ! ብለው ተናገሩት።
14ወረደም፥ የእግዚአብሔርም ሰው እንደ ተናገረው በዮርዳኖስ ሰባት ጊዜ ብቅ ጥልቅ አለ፤ ሥጋውም እንደ ገና እንደ ትንሽ ብላቴና ሥጋ ሆኖ ተመለሰ፥ ንጹሕም ሆነ።
15እርሱም ከጭፍራው ሁሉ ጋር ወደ እግዚአብሔር ሰው ተመለሰ፥ ወጥቶም በፊቱ ቆመና። እነሆ፥ ከእስራኤል ዘንድ በቀር በምድር ሁሉ አምላክ እንደሌለ አወቅሁ፤ አሁንም ከባሪያህ በረከት ትቀበል ዘንድ እለምንሃለሁ አለ።
16እርሱም። በፊቱ የቆምሁት ሕያው እግዚአብሔርን! አልቀበልም አለ። ይቀበለውም ዘንድ ግድ አለው፤ እርሱ ግን እንቢ አለ።
17ንዕማንም። እኔ ባሪያህ ከእንግዲህ ወዲህ ከእግዚአብሔር በቀር ለሌሎች አማልክት የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ሌላ መሥዋዕት አላቀርብምና ሁለት የበቅሎ ጭነት አፈር እንድወስድ እሺ ትለኝ ዘንድ እለምንሃለሁ።
18እግዚአብሔርም ለእኔ ለባሪያህ በዚህ ነገር ብቻ ይቅር ይበለኝ፤ ጌታዬ በዚያ ይሰግድ ዘንድ እጄን ተደግፎ ወደ ሬሞን ቤት በገባ ጊዜ፥ እኔም በሬሞን ቤት በሰገድሁ ጊዜ፥ እግዚአብሔር በዚህ ነገር ለእኔ ለባሪያህ ይቅር ይበለኝ አለ።
19እርሱም። በደኅና ሂድ አለው። አንድ አግድመትም ያህል ከእርሱ ራቀ።
20የእግዚአብሔርም ሰው ሎሌ ግያዝ። ጌታዬ ሶርያዊውን ይህን ንዕማንን ማረው፥ ካመጣለትም ነገር ምንም አልተቀበለም፤ ሕያው እግዚአብሔርን! በስተ ኋለው እሮጣለሁ፥ ከእርሱም አንዳች እወስዳለሁ አለ።
21ግያዝም ንዕማንን ተከተለው፤ ንዕማንም ወደ እርሱ ሲሮጥ ባየው ጊዜ ሊገናኘው ከሰረገላው ወርዶ። ሁሉ ደኅና ነውን? አለው።
22እርሱም። ደኅና ነው። አሁን ከነቢያት ወገን የሆኑት ሁለት ጕልማሶች ከተራራማው ከኤፍሬም አገር ወደ እኔ መጥተዋል፤ አንድ መክሊት ብርና ሁለት መለወጫ ልብስ ትሰጣቸው ዘንድ እለምንሃለሁ ብሎ ጌታዬ ላከኝ አለ።
23ንዕማንም። ሁለት መክሊት ትወስድ ዘንድ ይፈቀድልህ አለ፤ ግድ አለውም፤ ሁለቱንም መክሊት ብር በሁለት ከረጢት ውስጥ አሰረና ከሁለት መለወጫ ልብስ ጋር ለሁለት ሎሌዎቹ አስያዘ፤ እነርሱም ተሸክመው በፊቱ ሄዱ።
24ወደ ኮረብታውም በመጣ ጊዜ ከእጃቸው ወስዶ በቤቱ ውስጥ አኖራቸው፤ ሰዎቹንም አሰናበተ፥ እነርሱም ሄዱ።
25እርሱ ግን ገብቶ በጌታው ፊት ቆመ፤ ኤልሳዕም። ግያዝ ሆይ፥ ከወዴት መጣህ? አለው። እርሱም። እኔ ባሪያህ ወዴትም አልሄድሁም አለ።
26እርሱም። ያ ሰው ከሰረገላው ወርዶ ሊቀበልህ በተመለሰ ጊዜ ልቤ ከአንተ ጋር አልሄደምን? ብሩንና ልብሱን፥ የወይራውንና የወይኑን ቦታ፥ በጎችንና በሬዎችን፥ ወንዶችንና ሴቶችን ባሪያዎች ትቀበል ዘንድ ይህ ጊዜው ነውን?
27እንግዲህስ የንዕማን ለምጽ በአንተ ላይ፥ ለዘላለምም በዘርህ ላይ ይጣበቃል አለው። እንደ በረዶም ለምጻም ሆኖ ከእርሱ ዘንድ ወጣ።