ምዕራፍ 3
1ሰባተኛውም ወር በደረሰ ጊዜ፥ የእስራኤልም ልጆች በከተሞቻቸው ሳሉ፥ ሕዝቡ እንደ አንድ ሰው ሆነው ወደ ኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ።
2የኢዮሴዴቅም ልጅ ኢያሱ፥ ወንድሞቹም ካህናቱ፥ የሰላትያልም ልጅ ዘሩባቤል ወንድሞቹም ተነሥተው በእግዚአብሔር ሰው በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያቀርቡበት ዘንድ የእስራኤልን አምላክ መሠዊያ ሠሩ።
3በአገሩም ካሉት አሕዛብ ፈርተው ነበርና መሠዊያውን በስፍራው ላይ አስቀመጡት፥ በጥዋትና በማታም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቀረቡበት።
4እንደ ተጻፈውም የዳስ በዓል አደረጉ፤ እንደ ሥርዓቱም ለየዕለቱ የተገባውን የየዕለቱን የሚቃጠል መሥዋዕት በቍጥር አቀረቡ።
5ከዚያም በኋላ ዘወትር የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ የመባቻውንም መሥዋዕት፥ የተቀደሱትንም የእግዚአብሔር በዓላት ሁሉ መሥዋዕት፥ ሰውም ሁሉ ለእግዚአብሔር በፈቃድ የሰጠውን ቍርባን አቀረቡ።
6በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ማቅረብ ጀመሩ፤ የእግዚአብሔር መቅደስ ገና አልተመሠረተም ነበር።
7ለጠራቢዎችና ለአናጢዎችም ገንዘብ ሰጡ፤ የፋርስም ንጉሥ ቂሮስ እንደ ፈቀደላቸው የዝግባ ዛፍ ከሊባኖስ በባሕር ወደ ኢዮጴ ያመጡ ዘንድ ለሲዶናና ለጢሮስ ሰዎች መብልና መጠጥ ዘይትም ሰጡ።
8በኢየሩሳሌም ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ቤት በመጡ በሁለተኛው ዓመት በሁለተኛው ወር የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤል፥ የኢዩሴዴቅም ልጅ ኢያሱ፥ የቀሩትም ወንድሞቻቸው ካህናትና ሌዋውያን፥ ወደ ኢየሩሳሌምም የተመለሱት ምርኮኞች ሁሉ ጀመሩ፤ ሌዋውያንንም ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ የእግዚአብሔርን ቤት ሥራ እንዲያሠሩት ሾሙአቸው።
9ኢያሱም ልጆቹም ወንድሞቹም፥ የይሁዳም ልጆች ቀድምኤልና ልጆቹ፥ የኤንሐዳድም ልጆች፥ ልጆቻቸውና ወንድሞቻቸው ሌዋውያንም የእግዚአብሔርን ቤት የሚሠሩትን ያሠሩ ዘንድ በአንድነት ቆሙ።
10አናጢዎቹም የእግዚአብሔርን መቅደስ በመሠረቱ ጊዜ ካህናቱ ልብሳቸውን ለብሰው መለከቱን ይዘው፥ የአሳፍም ልጆች ሌዋውያን ጸናጽል ይዘው እንደ እስራኤል ንጉሥ እንደ ዳዊት ሥርዓት እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ዘንድ ቆሙ።
11ደግሞ። ቸር ነውና፥ ለእስራኤልም ምሕረቱ ለዘላለም ነውና እያሉ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑና እያከበሩ እርስ በእርሳቸው ያስተዛዝሉ ነበር፤ የእግዚአብሔርም ቤት ስለ ተመሠረተ ሕዝቡ ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ በታላቅ ድምፅ እልል አሉ።
12የፊተኛውን ቤት ያዩ ሽማግሌዎች የሆኑ ብዙ ካህናትና ሌዋውያን የአባቶችም ቤቶች አለቆች ግን ይህ መቅደስ በፊታቸው በተመሠረተ ጊዜ በታላቅ ድምፅ ያለቅሱ ነበር፤ ብዙ ሰዎችም በደስታ ይጮኹ ነበር፤
13ደስ ብሎአቸው የሚጮኹትን ድምፅ ከሕዝቡ ልቅሶ ድምፅ መለየት የሚችል አልነበረም፤ ሕዝቡም በታላቅ ድምፅ ይጮኽ ነበር፥ ድምፁም ከሩቅ ይሰማ ነበር።