ምዕራፍ 10
1ፍልስጥኤማውያንም ከእስራኤል ጋር ተዋጉ፤ የእስራኤልም ሰዎች ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፥ ተወግተውም በጊልቦአ ተራራ ላይ ወደቁ።
2ፍልስጥኤማውያንም ሳኦልንና ልጆቹን በእግር በእግራቸው ተከትለው አባረሩአቸው፤ ፍልስጥኤማውያንም የሳኦልን ልጆች ዮናታንንና አሚናዳብን ሜልኪሳንም ገደሉ።
3ሰልፍም በሳኦል ላይ ጠነከረ፥ ቀስተኞችም አገኙት፤ ከቀስተኞችም የተነሣ ተጨነቀ።
4ሳኦልም ጋሻ ጃግሬውን። እነዚህ ቈላፋን መጥተው እንዳይዘብቱብኝ ሰይፍህን መዝዘህ ውጋኝ አለው። ጋሻ ጃግሬው ግን እጅግ ፈርቶ ነበርና እንቢ አለ። ሳኦልም ሰይፉን ወስዶ በላዩ ወደቀ።
5ጋሻ ጃግሬውም ሳኦል እንደ ሞተ ባየ ጊዜ እርሱ ደግሞ በሰይፉ ላይ ወድቆ ሞተ።
6ሳኦልና ሦስቱ ልጆቹ የቤቱም ሰዎች ሁሉ በአንድ ላይ ሞቱ።
7በሸለቆውም የነበሩት የእስራኤል ሰዎች ሁሉ እንደ ሸሹ፥ ሳኦልና ልጆቹም እንደ ሞቱ ባዩ ጊዜ ከተሞቻቸውን ለቅቀው ሸሹ፤ ፍልስጥኤማውያንም መጥተው ተቀመጡባቸው።
8በነጋውም ፍልስጥኤማውያን የሞቱትን ለመግፈፍ በመጡ ጊዜ ሳኦልንና ልጆቹን በጊልቦአ ተራራ ላይ ወድቀው አገኙአቸው።
9ገፈፉትም፥ ራሱንና መሣሪያውንም አንሥተው ለጣኦቶቻቸውና ለሕዝቡ የምሥራች ይወስዱ ዘንድ ወደ ፍልስጥኤማውያን አገር ዙሪያ ሰደዱ።
10መሣሪያውንም በአምላኮቻቸው ቤት ውስጥ አኖሩ፤ ራሱንም በዳጎን ቤት ውስጥ ቸነከሩት።
11የኢያቢስ ገለዓድም ሰዎች ሁሉ ፍልስጥኤማውያን በሳኦል ላይ ያደረጉትን ሁሉ በሰሙ ጊዜ፥
12ጽኑአን ሰዎች ሁሉ ተነሥተው የሳኦልን ሬሳ የልጆቹንም ሬሳ ወሰዱ፥ ወደ ኢያቢስም አመጡአቸው፤ በኢያቢስም ካለው ከትልቁ ዛፍ በታች አጥንቶቻቸውን ቀበሩ፥ ሰባት ቀንም ጾሙ።
13እንዲሁ ሳኦል በእግዚአብሔር ላይ ስላደረገው ኃጢአት፥ የእግዚአብሔርንም ቃል ስላልጠበቀ ሞተ። ደግሞም መናፍስት ጠሪ
14ስለ ጠየቀ እግዚአብሔርንም ስላልጠየቀ፥ ስለዚህ ገደለው፥ መንግሥቱንም ወደ እሴይ ልጅ ወደ ዳዊት አሳለፈው።