ምዕራፍ 12
1በጺቅላግም ከቂስ ልጅ ከሳኦል በተሸሸገ ጊዜ ወደ ዳዊት የመጡ እነዚህ ናቸው፤ በሰልፍም ባገዙት ኃያላን መካከል ነበሩ።
2ቀስተኞችም ነበሩ፥ በቀኝና በግራም እጃቸው ድንጋይ ሊወነጭፉ ፍላጻም ሊወረውሩ ይችሉ ነበር፤ ከብንያም ወገን የሳኦል ወንድሞች ነበሩ።
3አለቃቸው አሒዔዝር ነበረ፥ ከእርሱም በኋላ ኢዮአስ፥ የጊብዓዊው የሸማዓ ልጆች፤ ይዝኤል፥ ፋሌጥ፥ የዓዝሞት ልጆች፤ በራኪያ፥ ዓናቶታዊው ኢዩ፥
4ገባዖናዊው ሰማያስ፥ እርሱ በሠላሳው መካከልና በሠላሳው ላይ ኃያል ሰው ነበረ፤ ኤርምያስ፥ የሕዚኤል፥ ዮሐናን፥
5ገድሮታዊው ዮዛባት፥ ኤሉዛይ፥ ኢያሪሙት፥ በዓልያ፥ ሰማራያ፥ ሀሩፋዊው ሰፋጥያስ፥
6ቆርያውያን ሕልቃና፥ ይሺያ፥ አዛርኤል፥ ዮዛር፥ ያሾቢአም፤
7የጌዶር ሰው የይሮሃም ልጆች የኤላ፥ ዝባድያ
8ዳዊትም ከምድረ በዳ ውስጥ ባለችው በአንባይቱ ሳለ ከጋድ ወገን የሆኑ እነዚህ ጋሻና ጦር የሚይዙ፥ ጽኑዓን ኃያላን፥ ሰልፈኞች፥ ወደ እርሱ ተጠጉ፤ ፊታቸውም እንደ አንበሳ ፊት ነበረ፥ በተራራም ላይ እንደሚዘልል ሚዳቋ ፈጣኖች ነበሩ።
9አለቃው ዔጼር፥ ሁለተኛው አብድዩ፥
10ሦስተኛው ኤልያብ፥ አራተኛው መስመና፥
11አምስተኛው ኤርምያስ፥ ስድስተኛው አታይ፥
12ሰባተኛው ኤሊኤል፥ ስምንተኛው ዮሐናን፥
13ዘጠነኛው ኤልዛባድ፥ አሥረኛው ኤርምያስ፥ አሥራ አንደኛው መክበናይ።
14እነዚህ የጋድ ልጆች የጭፍራ አለቆች ነበሩ፤ ከእነርሱም ታናሹ ከመቶ፥ ታላቁ ከሺህ ይመዛዘኑ ነበር።
15በመጀመሪያው ወር ዮርዳኖስ ከዳር እስከ ዳር ሞልቶ በነበረ ጊዜ የተሻገሩት እነዚህ ናቸው፤ በሸለቆውም ውስጥ በምሥራቅና በምዕራብ በኩል የተቀመጡትን ሁሉ አባረሩ።
16ዳዊትም ወደነበረባት ወደ አምባይቱ ከብንያምና ከይሁዳ ወገን ሰዎች መጡ።
17ዳዊትም ሊገናኛቸው ወጥቶ። ትረዱኝ ዘንድ በሠላም ወደ እኔ መጥታችሁ እንደ ሆነ ልቤ ከእናንተ ጋር አንድ ይሆናል፤ ለጠላቶቼ አሳልፋችሁ ልትሰጡኝ መጥታችሁ እንደሆነ ግን፥ በእጄ ዓመፅ የለብኝምና የአባቶቻችን አምላክ ይመልከተው፥ ይፍረደውም አላቸው።
18መንፈስም በሠላሳው አለቃ በአማሳይ ላይ መጣ፥ እርሱም። ዳዊት ሆይ፥ እኛ የአንተ ነን፤ የእሴል ልጅ ሆይ፥ እኛ ከአንተ ጋር ነን፤ አምላክህ ይረዳሃልና ሰላም ሰላም ለአንተ ይሁን፥ ለሚረዱህም ሰላም ይሁን አለ። ዳዊትም ተቀበላቸው፥ የጭፍራም አለቆች አደረጋቸው።
19ዳዊትም ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሳኦልን ሊወጋ በመጣ ጊዜ ከምናሴ ወገን ሰዎች ወደ ዳዊት ከዱ፤ የፍልስጥኤማውያን አለቆች ግን። በራሳችን ላይ ጕዳት አድርጎ ወደ ጌታው ወደ ሳኦል ይመለሳል ሲሉ ተማክረው ሰድደውታልና እነርሱ አልረዷቸውም።
20ወደ ጺቅላግም ሲሄድ ከምናሴ ወገን የምናሴ ሻለቆች የነበሩ ዓድና፥ ዮዛባት፥ ይዲኤል፥ ሚካኤል፥ ዮዛባት፥ ኤሊሁ፥ ጺልታይ ወደ እርሱ ከዱ።
21ሁሉም ጽኑዓን ኃያላንና በሠራዊቱ ላይ አለቆች ነበሩና በአደጋ ጣዮቹ ላይ ዳዊትን አገዙት።
22እንደ እግዚአብሔርም ሠራዊት ታላቅ ሠራዊት እስኪሆን ድረስ ዳዊትን ለመርዳት ዕለት ዕለት ይመጡ ነበር።
23እንደ እግዚአብሔርም ቃል የሳኦልን መንግሥት ወደ እርሱ ይመልሱ ዘንድ በኬብሮን ሳለ ወደ ዳዊት የመጡት የሠራዊቱ አለቆች ቍጥር ይህ ነው።
24ጋሻና ጦር ተሸክመው ለሰልፍ የተዘጋጁ የይሁዳ ልጆች ስድስት ሺህ ስምንት መቶ ነበሩ።
25ለሰልፍ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች የነበሩ የስምዖን ልጆች ሰባት ሺህ አንድ መቶ ነበሩ።
26የሌዊ ልጆች አራት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ።
27የአሮንም ቤት አለቃ ዮዳሄ ነበረ፥ ከእርሱም ጋር ሦስት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ፤
28ከእርሱም ጋር ጽኑዕ ኃያል ጕልማሳ ሳዶቅ ነበረ፥ ከአባቱም ቤት ሃያ ሁለት አለቆች ነበሩ።
29የሳኦልም ወንድሞች ከሆኑ ከብንያም ወንድሞች የሚበልጠው ክፍል እስከዚያ ዘመን ድረስ የሳኦልን ቤት ይከተል ነበርና ከእነርሱ ዘንድ የመጡ ሦስት ሺህ ነበሩ።
30ጽኑዓን ኃያላን የሆኑ በአባቶቻቸውም ቤት የታወቁ የኤፍሬም ልጆች ሀያ ሺህ ስምንት መቶ ነበሩ።
31በየስማቸውም የተጻፉ ዳዊትን ያነግሡት ዘንድ የመጡ የምናሴ ነገድ እኵሌታ አሥራ ስምንት ሺህ ነበሩ።
32እስራኤልም የሚገባውን ያደርግ ዘንድ ዘመኑን የሚያውቁ ጥበበኞች ሰዎች የይሳኮር ልጆች አለቆች ሁለት መቶ ነበሩ፤ ወንድሞቻቸውም ሁሉ ይታዘዙአቸው ነበር።
33በጭፍራውም ውስጥ የወጡ ለሰልፍም የተዘጋጁ፥ የማያመነቱ፥ መሣሪያም ሁሉ የያዙ የዛብሎን ሰዎች አምሳ ሺህ ነበሩ።
34የንፍታሌምም አለቆች አንድ ሺህ ነበሩ፥ ከእነርሱም ጋር ጋሻና ጦር የሚይዙ ሠላሳ ሰባት ሺህ ነበሩ።
35ለሰልፍም የተዘጋጁ የዳን ሰዎች ሃያ ስምንት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ።
36በጭፍራውም ውስጥ የሚወጡ፥ ለሰልፍም የተዘጋጁ የአሴር ሰዎች አርባ ሺህ ነበሩ።
37በዮርዳኖስም ማዶ ካሉ ከሮቤልና ከጋድ ሰዎች ከምናሴም ነገድ እኵሌታ መሣሪያን ሁሉ ይዘው የመጡ መቶ ሀያ ሺህ ነበሩ።
38እነዚህ ሁሉ ዳዊትን በእስራኤል ሁሉ ላይ ያነግሡት ዘንድ አርበኞችና ሰልፈኞች እየሆኑ በፍጹም ልባቸው ወደ ኬብሮን መጡ፤ ደግሞም ከእስራኤል የቀሩት ሁሉ ዳዊትን ያነግሡት ዘንድ አንድ ልብ ነበሩ።
39ወንድሞቻቸውም አዘጋጅተውላቸው ነበርና እየበሉና እየጠጡ በዚያ ከዳዊት ጋር ሦስት ቀን ተቀመጡ።
40ደግሞም በእስራኤል ዘንድ ደስታ ሆኖአልና እስከ ይሳኮርና እስከ ዛብሎን እስከ ንፍታሌምም ድረስ ለእርሱ አቅራቢያ የነበሩ በአህያና በግመል በበቅሎና በበሬ ላይ እንጀራና ዱቄት የበለስ ጥፍጥፍና የዘቢበ ዘለላ የወይንም ጠጅ ዘይትም በሬዎችንና በጎችንም በብዙ አድርገው ያመጡ ነበር።