English

ምዕራፍ 14

1የጢሮስም ንጉሥ ኪራም ቤት ይሠሩለት ዘንድ መልእክተኞችን የዝግባ እንጨትንም ጠራቢዎችንም አናጢዎችንም ወደ ዳዊት ላከ።
2ስለ ሕዝቡም ስለ እስራኤል መንግሥቱ ከፍ ብሎአልና እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርጎ እንዳጸናው ዳዊት አወቀ።
3ዳዊትም በኢየሩሳሌም ሚስቶችን ጨምሮ ሌሎችን ወንዶችንና ሴቶችን ልጆች ወለደ።
4በኢየሩሳሌምም የወለዳቸው የልጆቹ ስም ይህ ነው፤ ሳሙስ፥
5ሶባብ፥ ናታን፥ ሰሎሞን፥ ኢያቤሐር፥ ኤሊሱዔ፥
6ኤሊፋላት፥ ኖጋ፥ ናፌቅ፥ ያፍያ፥
7ኤሊሳማ፥ ኤሊዳሄ፥ ኤሊፋላት።
8ፍልስጥኤማውያንም ዳዊት በእስራኤል ሁሉ ላይ ንጉሥ ሆኖ እንደተቀባ ሰሙ፥ ፍልስጥኤማውያንም ሁሉ ዳዊትን ሊፈልጉ ወጡ፤ ዳዊትም በሰማ ጊዜ ሊጋጠማቸው ወጣ።
9ፍልስጥኤማውያንም መጥተው በራፋይም ሸለቆ አደጋ ጣሉ።
10ዳዊትም። ወደ ፍልስጥኤማውያን ልውጣን? በእጄስ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህን? ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም። በእጅህ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁና ውጣ አለው።
11ወደ በአልፐራሲም ወጡ፥ በዚያም ዳዊት መታቸው። ዳዊትም። ውኃ እንዲያፈርስ እግዚአብሔር ጠላቶቼን በእጄ አፈረሳቸው አለ። ስለዚህም የዚያን ስፍራ ስም በአልፐራሲም ብለው ጠሩት።
12አማልክቶቻቸውንም በዚያ ተዉ፤ ዳዊትም አዘዘ፥ በእሳትም አቃጠሏቸው።
13ፍልስጥኤማውያንም ደግሞ በሸለቆው አደጋ ጣሉ።
14ዳዊትም እንደ ገና እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም። ከእነርሱ ዞረህ በሾላው ዛፍ ፊት ለፊት ግጠማቸው እንጂ ወደ እነርሱ አትውጣ።
15በሾላውም ዛፍ እራስ ውስጥ የሽውሽውታ ድምፅ ስትሰማ የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ ሊመታ እግዚአብሔር በፊትህ ይወጣልና በዚያን ጊዜ ወደ ሰልፍ ውጣ አለው።
16ዳዊትም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ከገባዖንም ጀምሮ እስከ ጌዝር ድረስ የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ መቱት።
17የዳዊትም ዝና በየአገሩ ሁሉ ወጣ፤ መፈራቱንም እግዚአብሔር በአሕዛብ ሁሉ ዘንድ አደረገው።