English

ምዕራፍ 36

1የአገሩም ሰዎች የኢዮስያስን ልጅ ኢዮአክስን ወስደው በአባቱ ፋንታ በኢየሩሳሌም አነገሡት።
2ኢዮአክስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ ሦስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ሦስት ወር ነገሠ።
3የግብጽም ንጉሥ በኢየሩሳሌም ከመንግሥቱ አወጣው፥ መቶም መክሊት ብርና አንድ መክሊት ወርቅ ዕዳ ጣለበት።
4የግብጽም ንጉሥ ወንድሙን ኤልያቄምን በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አነገሠ፥ ስሙንም ኢዮአቄም ብሎ ለወጠ፤ ኒካዑም ወንድሙን ኢዮአክስን ይዞ ወደ ግብፅ ወሰደው።
5ኢዮአቄምም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አምስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አሥራ አንድ ዓመት ነገሠ፤ በአምላኩም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።
6የባቢሎንም ንጉሥ ናቡከደነፆር በእርሱ ላይ መጥቶ ወደ ባቢሎን ይወስደው ዘንድ በሰንሰለት አሰረው።
7ናቡከደነፆርም ከእግዚአብሔር ቤት ዕቃ አያሌውን ወደ ባቢሎን አፈለሰ፥ በባቢሎንም በመቅደሱ ውስጥ አኖረው።
8የቀረውም የኢዮአቄም ነገር፥ ያደረገውም ርኵሰት፥ በእርሱም የተገኘው ሁሉ፥ እነሆ፥ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል፤ ልጁም ዮአኪን በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
9ዮአኪንም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የአሥራ ስምንት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ሦስት ወርና አሥር ቀን ነገሠ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ።
10ዓመቱ ባለፈ ጊዜ ንጉሡ ናቡከደነፆር ልኮ ወደ ባቢሎን ወሰደው፥ የከበረውንም የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃ ከእርሱ ጋር አስወሰደ፤ ወንድሙንም ሴዴቅያስን በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አነገሠ።
11ሴዴቅያስ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አንድ ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አሥራ አንድ ዓመት ነገሠ።
12በአምላኩም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፤ በእግዚአብሔርም አፍ በተናገረው በነቢዩ በኤርሚያስ ፊት ራሱን አላወረደም።
13ደግሞም በእግዚአብሔር አምሎት በነበረው በንጉሡ በናቡከደነፆር ላይ ዐመፀ፤ ወደ እስራኤልም አምላክ ወደ እግዚአብሔር እንዳይመለስ አንገቱን አደነደነ ልቡንም አጠነከረ።
14ደግሞም የካህናቱ አለቆች ሁሉ ሕዝቡም እንደ አሕዛብ ያለ ርኵሰት ሁሉ መተላለፍን አበዙ፤ በኢየሩሳሌምም የቀደሰውን የእግዚአብሔርን ቤት አረከሱ።
15የአባቶቻቸውም አምላክ እግዚአብሔር ለሕዝቡና ለማደሪያው ስላዘነ ማለዳ ተነሥቶ በመልእክተኞቹ እጅ ወደ እነርሱ ይልክ ነበር።
16እነርሱ ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በሕዝቡ ላይ እስኪወጣ ድረስ፥ ፈውስም እስከማይገኝላቸው ድረስ፥ በእግዚአብሔር መልእክተኞች ይሳለቁ፥ ቃሉንም ያቃልሉ፥ በነቢያቱም ላይ ያፌዙ ነበር።
17ስለዚህም የከለዳውያንን ንጉሥ አመጣባቸው፤ እርሱም ጕልማሶቻቸውን በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሰይፍ ገደላቸው፤ ጕልማሳውንና ቈንጆይቱን ሽማግሌውንና አሮጌውን አልማረም፤ ሁሉንም በእጁ አሳልፎ ሰጠው።
18የእግዚአብሔርንም ቤት ዕቃ ሁሉ ታላቁንና ታናሹን፥ የእግዚአብሔርንም ቤት መዝገብ፥ የንጉሡንና የአለቆቹን መዝገብ፥ እነዚህን ሁሉ ወደ ባቢሎን ወሰደ።
19የእግዚአብሔርንም ቤት አቃጠሉ፥ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር አፈረሱ፥ አዳራሾችዋንም በእሳት አቃጠሉ፥ መልካሙንም ዕቃዋን ሁሉ አጠፉ።
20ከሰይፍም ያመለጡትን ወደ ባቢሎን ማረካቸው፤ የፋርስ ንጉሥም እስኪነግሥ ድረስ ለንጉሡና ለልጆቹ ባሪያዎች ሆኑ፤
21በኤርምያስም አፍ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል እንዲፈጸም፥ ምድሪቱ ሰንበትን በማድረግዋ እስክታርፍ ድረስ፤ በተፈታችበትም ዘመን ሁሉ፥ ሰባ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ፥ ሰንበትን አገኘች።
22በኤርምያስም አፍ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት እግዚአብሔር የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አስነሣ፤ እርሱም። የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል።
23የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤ በይሁዳም ባለችው በኢየሩሳሌም ቤት እሠራለት ዘንድ አዝዞኛል፤ ከሕዝቡ ሁሉ በእናንተ ዘንድ ማንም ቢሆን አምላኩ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ይሁን፥ እርሱም ይውጣ ብሎ በመንግሥቱ ሁሉ አዋጅ አስነገረ፥ ደግሞም በጽሕፈት አደረገው።