English

ምዕራፍ 5

1አቤቱ፥ የሆነብንን አስብ፤ ተመልከት ስድባችንንም እይ።
2ርስታችን ለእንግዶች፥ ቤቶቻችን ለሌሎች ሆኑ።
3ድሀ አደጎችና አባት የሌለን ሆነናል፤ እናቶቻችን እንደ መበለቶች ሆነዋል።
4ውኃችንን በብር ጠጣን እንጨታችንን በዋጋ ገዛን።
5አሳዳጆቻችን በአንገታችን ላይ ናቸው፤ እኛ ደክመናል ዕረፍትም የለንም።
6ለግብጻውያንና ለአሦራውያን እንጀራ እንጠግብ ዘንድ እጅ ሰጠን።
7አባቶቻችን ኃጢአትን ሠሩ ዛሬም የሉም፤ እኛም በደላቸውን ተሸከምን።
8ባሪያዎች ሠልጥነውብናል፤ ከእጃቸው የሚታደገን የለም።
9ከምድረ በዳ ሰይፍ የተነሣ በሕይወታችን እንጀራችንን እናመጣለን።
10ከሚያቃጥል ከራብ ትኩሳት የተነሣ ቁርበታችን እንደ ምድጃ ጠቈረ።
11በጽዮን ሴቶችን፥ በይሁዳም ከተሞች ደናግልን አጐሰቈሉ።
12አለቆች በእጃቸው ተሰቀሉ፤ የሽማግሌዎች ፊት አልታፈረም።
13ጕልማሶች ወፍጮን ተሸከሙ፥ ልጆችም ከእንጨት በታች ተሰናከሉ።
14ሽማግሌዎች ከአደባባይ፥ ጕልማሶች ከበገናቸው ተሻሩ።
15የልባችን ደስታ ቀርቶአል፤ ዘፈናችን ወደ ልቅሶ ተለውጦአል።
16አክሊል ከራሳችን ወድቆአል፤ ኃጢአት ሠርተናልና ወዮልን!
17ስለዚህ ልባችን ታምሞአል፤ ስለዚህም ነገር ዓይናችን ፈዝዞአል፤
18ስለ ጽዮን ተራራ፥ ባድማ ሆናለችና፥ ቀበሮችም ተመላልሰውባታልና።
19አቤቱ፥ አንተ ለዘላለም ትኖራለህ፤ ዙፋንህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ነው።
20ስለ ምን ለዘላለም ትረሳናለህ? ስለ ምንስ ለረጅም ዘመን ትተወናለህ?
21አቤቱ፥ ወደ አንተ መልሰን እኛም እንመለሳለን፤ ዘመናችንን እንደ ቀድሞ አድስ።
22ነገር ግን ፈጽመህ ጥለኸናል፤ እጅግ ተቈጥተኸናል።