English

ምዕራፍ 15

1ስለ ሞዓብ የተነገረ ሸክም። የሞዓብ ዔር በሌሊት ፈርሶ ጠፋ፤ ቂር የሚባልም የሞዓብ ምሽግ በሌሊት ፈርሶ ጠፋ።
2ወደ ባይት ወደ ዲቦንም ወደ ኮረብታ መስገጃዎችም ለልቅሶ ወጥተዋል፤ ሞዓብ በናባው በሜድባ ላይ ታለቅሳለች፤ ራሳቸው ሁሉ ተነጭቶአል፥ ጢማቸውም ሁሉ ተላጭቶአል።
3በየመገዳቸውም በማቅ ታጥቀዋል፤ በየሰገነቶቻቸውና በየአደባባዮቻቸው እንባ እጅግ እያፈሰሱ ሁሉም አልቅሰዋል።
4ሐሴቦንና ኤልያሊ ጮኹ፤ ድምፃቸው እስከ ያሀጽ ድረስ ይሰማል፤ ስለዚህ የሞዓብ ሰልፈኞች ጮኹ፤ ነፍስዋ በውስጥዋ ተንቀጠቀጠች።
5ልቤ ስለ ሞዓብ ጮኸ፤ ከእርስዋም የሚሸሹ ወደ ዞዓር ወደ ዔግላት ሺሊሺያ ኰበለሉ፤ በሉሒት ዓቀበት ላይ እያለቀሱ ይወጣሉ፥ በሖሮናይምም መንገድ የዋይታ ጩኸት ያነሣሉ።
6የኔምሬም ውኆች ይደርቃሉ፤ ሣሩም ደርቋል፥ ለጋውም ጠውልጓል፥ ልምላሜውም ሁሉ የለም።
7ስለዚህ የሰበሰቡትን ሀብትና መዝገባቸውን ወደ አኻያ ዛፍ ወንዝ ማዶ ይወስዱታል።
8ጩኸት የሞዓብን ዳርቻ ሁሉ ዞረ፤ ልቅሶዋም ወደ ኤግላይምና ወደ ብኤርኢሊም ደረሰ።
9የዲሞንም ውኃ ደም ተሞልታለች፤ በዲሞንም ላይ ሥቃይን እጨምራለሁ፥ ከሞዓባውያንም በሚያመልጡ፥ ከምድርም በሚቀሩ ላይ አንበሳን አመጣለሁ።