English

ምዕራፍ 3

1እነሆ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ ድጋፍንና ብርታትን፥ የእንጀራን ድጋፍ ሁሉ የውኃውንም ድጋፍ ሁሉ፥
2ኃያሉንም፥ ተዋጊውንም፥ ፈራጁንም፥ ነቢዩንም፥ ምዋርተኛውንም፥
3ሽማግሌውንም፥ የአምሳ አለቃውንም፥ ከበርቴውንም፥ አማካሪውንም፥ ብልሁንም ሠራተኛ፥ አስማት አዋቂውንም ይነቅላል።
4አለቆቻቸው እንዲሆኑ ብላቴኖችን አስነሣባቸዋለሁ፥ ሕፃናቶችም ይገዙአቸዋል።
5ሕዝቡም፥ ሰው በሰው ላይ ሰውም በባልንጀራው ላይ፥ ይገፋፋል፤ ብላቴናውም በሽማግሌው ላይ የተጠቃውም በከበርቴው ላይ ይኰራል።
6ሰውም በአባቱ ቤት ውስጥ ወንድሙን ይዞ። አንተ ልብስ አለህ አለቃም ሁንልን ይህችም ባድማ ከእጅህ በታች ትሁን ሲለው፥
7በዚያ ቀን ድምፁን ከፍ አድርጎ። እኔ በቤቴ ውስጥ እንጀራ ወይም ልብስ የለኝምና ባለ መድኃኒት አልሆንም፤ በሕዝቡም ላይ አለቃ አታደርጉኝም ይላል።
8የክብሩን ዓይን ያስቈጡ ዘንድ ምላሳቸውና ሥራቸው በእግዚአብሔር ላይ ነውና ኢየሩሳሌም ተፈታች ይሁዳም ወደቀ።
9የፊታቸውም እፍረት ይመሰክርባቸዋል፤ እንደ ሰዶምም ኃጢአታቸውን ያወራሉ፥ አይሠውሩአትም። በራሳቸው ላይ ክፉ ነገርን ሠርተዋልና ለነፍሳቸው ወዮ!
10የሥራቸውን ፍሬ ይበላሉና ጻድቁን። መልካም ይሆንልሃል በሉት።
11እንደ እጁ ሥራ ፍዳው ይደረግበታልና ለበደለኛ ወዮ! ክፉም ደርሶበታል።
12ሕዝቤንስ አስገባሪዎቻቸው ይገፉአቸዋል፥ አስጨናቂዎችም ይሠለጥኑባቸዋል። ሕዝቤ ሆይ፥ የመሩአችሁ ያስቱአችኋል የምትሄዱበትንም መንገድ ያጠፋሉ።
13እግዚአብሔር ለፍርድ ተነሥቶአል በሕዝቡም ላይ ሊፈርድ ቆሞአል።
14እግዚአብሔር ከሕዝቡ ሽማግሌዎችና ከአለቆቻቸው ጋር ይፋረዳል፤ የወይኑን ቦታ የጨረሳችሁ እናንተ ናችሁ፤ ከድሆች የበዘበዛችሁት በቤታችሁ አለ፤
15ሕዝቤንም ለምን ታደቅቁአቸዋላችሁ? የድሆችንስ ፊት ለምን ትፈጫላችሁ? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
16ደግሞም እግዚአብሔር እንዲህ አለ። የጽዮን ቈነጃጅት ኰርተዋልና፥ አንገታቸውንም እያሰገጉ በዓይናቸውም እያጣቀሱ፥ ፈንጠርም እያሉ፥ በእግራቸውም እያቃጨሉ ይሄዳሉና
17ስለዚህ ጌታ የጽዮንን ቈነጃጅት አናት በቡሀነት ይመታል፥ እግዚአብሔርም ኀፍረተ ሥጋቸውን ይገልጣል።
18በዚያም ቀን ጌታ የእግር አልቦውን ክብር፥ መርበብንም፥ ጨረቃ የሚመስለውንም ጌጥ፥ የጆሮ እንጥልጥሉንም፥
19አንባሩንም፥ መሸፈኛውንም፥ ቀጸላውንም፥
20ሰንሰለቱንም፥ መቀነቱንም፥ የሽቱውንም ዕቃ፥
21አሸንክታቡንም፥ የእጅና የአፍንጫ ቀለበቱንም፥
22የዓመት በዓልንም ልብስ፥ መጐናጸፊያውንም፥ ልግምበገላውንም፥ ከረጢቱንም፥
23መስተዋቱንም፥ ከጥሩ በፍታ የተሰራውንም ልብስ፥ ራስ ማሰሪያውንም፥ ዓይነ ርግቡንም ያስወግዳል።
24እንዲህም ይሆናል፤ በሽቱ ፋንታ ግማት፥ በመታጠቂያውም ፋንታ ገመድ፥ ጠጕርንም በመንቀስ ፋንታ ቡሀነት፥ በመጐናጸፊያ ፋንታ ማቅ፥ በውበትም ፋንታ ጠባሳ ይሆናል።
25ጕልማሶችሽ በሰይፍ፥ ኃያላንሽም በውጊያ ይወድቃሉ።
26በሮችዋ ያዝናሉ ያለቅሱማል፤ እርስዋም ብቻዋን በምድር ላይ ትቀመጣለች።