English

ምዕራፍ 35

1ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ደስ ይላቸዋል፥ በረሀውም ሐሤት ያደርጋል እንደ ጽጌ ረዳም ያብባል።
2እጅግ ያብባል በደስታና በዝማሬ ሐሤትን ያደርጋል፤ የሊባኖስ ክብር፥ የቀርሜሎስና የሳሮን ግርማ ይሰጠዋል፤ የእግዚአብሔርንም ክብር የአምላካችንንም ግርማ ያያሉ።
3የደከሙትን እጆች አበርቱ፥ የላሉትንም ጕልበቶች አጽኑ።
4ፈሪ ልብ ላላቸው። እነሆ፥ አምላካችሁ በበቀል በእግዚአብሔርም ብድራት ይመጣልና፥ መጥቶም ያድናችኋልና በርቱ፥ አትፍሩ በሉአቸው።
5በዚያን ጊዜም የዕውሮች ዓይን ይገለጣል፤ የደንቆሮችም ጆሮ ይከፈታል።
6በዚያን ጊዜ አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘልላል፥ የድዳም ምላስ ይዘምራል፤ በምድረ በዳ ውኃ፥ በበረሀም ፈሳሽ ይፈልቃልና።
7ደረቂቱ ምድር ኵሬ፥ የጥማት መሬት የውኃ ምንጭ ትሆናለች፤ ቀበሮ የተኛበት መኖሪያ ልምላሜና ሸምበቆ ደንገልም ይሆንበታል።
8በዚያም ጐዳናና መንገድ ይሆናል እርሱም የተቀደሰ መንገድ ይባላል፤ ንጹሐንም ያልሆኑ አያልፉበትም፥ ለንጹሐን ግን ይሆናል፤ ተላላፊዎችና ሰነፎች እንኳ አይስቱበትም።
9አንበሳም አይኖርበትም፥ ነጣቂ አውሬም አይወጣበትም፥ ከዚያም አይገኙም፤ የዳኑት ግን በዚያ ይሄዳሉ፤
10እግዚአብሔርም የተቤዣቸው ይመለሳሉ እየዘመሩም ወደ ጽዮን ይመጣሉ፤ የዘላለም ደስታ በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ሐሤትንና ደስታን ያገኛሉ፥ ኀዘንና ትካዜም ይሸሻሉ።