English

ምዕራፍ 15

1በየሰባቱ ዓመት መጨረሻ የዕዳ ምሕረት ታደርጋለህ።
2ለምሕረቱም የሚገባ ወግ ይህ ነው፤ አበዳሪ ሁሉ ለባልንጀራው ያበደረውን ይተዋል፤ የእግዚአብሔር ይቅርታ ታውጆአልና ያበደረውን ከባልንጀራው ወይም ከወንድሙ አይሻ።
3ከእንግዳ ላይ ያበደርኸውን መፈለግ ትችላለህ፤ በወንድምህ ላይ ያለውን ሁሉ ግን እጅህ ይተወዋል።
4
5አምላክህም እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ ርስት አድርጎ በሰጠህ ምድር ላይ እግዚአብሔር በእውነት ይባርክሃልና አንተ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ፈጽመህ ብትሰማ፥ ታደርጋትም ዘንድ ዛሬ የማዝዝህን ይህችን ትእዛዝ ሁሉ ብትጠብቅ፥ በመካከልህ ድሀ አይኖርም።
6አምላክህም እግዚአብሔር ተስፋ እንደ ሰጠህ ይባርክሃል፤ ለብዙ አሕዛብም ታበድራለህ፥ አንተ ግን አትበደርም፤ ብዙ አሕዛብንም ትገዛለህ፥ አንተን ግን አይገዙህም።
7አምላክህ እግዚአብሔር በሰጠህ በአገርህ ደጅ ውስጥ ከሚኖሩ ከወንድሞችህ አንዱ ቢደኸይ፥ ልብህን አታጽና፥ በድሀው ወንድምህ ላይ እጅህን አትጨብጥ።
8ነገር ግን እጅህን ለእርሱ ክፈት፥ የለመነህንም አስፈላጊውን ነገር አበድረው።
9ሰባተኛው ዓመት የዕዳ ምሕረት ዓመት ቀርቦአል ብለህ ክፉ አሳብ በልብህ እንዳታስብ፥ ለድሀውም ወንድምህ አንዳች የማትሰጥ እንዳትሆን፥ ዓይንህም በእርሱ ላይ ክፉ እንዳይሆን፥ እርሱም ወደ እግዚአብሔር በአንተ ላይ እንዳይጮህ፥ ኃጢአትም እንዳይሆንብህ ተጠንቀቅ።
10እጅህን በምትጥልበት ሁሉ አምላክህ እግዚአብሔር ስለዚህ በሥራህ ሁሉ ይባርክሃልና ፈጽመህ ስጠው፥ በሰጠኸውም ጊዜ በልብህ አትጸጸት።
11ድሆች ከምድሪቱ ላይ አያልቁምና ስለዚህ እኔ። በአገርህ ውስጥ ላለው ድሀ ለተቸገረውም ወንድምህ እጅህን ትከፍታለህ ብዬ አዝዝሃለሁ።
12አንተም ወንድምህን ዕብራዊውን ወይም ዕብራዊቱን ብትገዛ ስድስት ዓመት ያገልግሉህ፤ በሰባተኛውም ዓመት ከአንተ ዘንድ አርነት አውጣው።
13ከአንተም ዘንድ አርነት ባወጣኸው ጊዜ ባዶውን አትስደደው፤
14ነገር ግን ከመንጋህ፥ ከአውድማህም፥ ከወይንህም መጥመቂያ ትለግስለታለህ፤ አምላክህ እግዚአብሔር እንደ ባረከህ መጠን ትሰጠዋለህ።
15አንተም በግብፅ ምድር ባሪያ እንደ ነበርህ አምላክህም እግዚአብሔር እንዳዳነህ አስብ፤ ስለዚህ እኔ ዛሬ ይህን ነገር አዝዝሃለሁ።
16እርሱ ግን አንተንና ቤትህን ስለወደደ፥ ከአንተም ጋር መልካም ስለ ሆነለት። ልወጣ አልወድድም ቢል፥
17አንተ ወስፌ ወስደህ በቤትህ በር ላይ ጆሮውን ትበሳዋለህ፥ ለዘላለምም ባሪያ ይሆንልሃል። በሴት ባሪያህ ደግሞ እንዲሁ ታደርጋለህ።
18እርሱንም አርነት ባወጣኸው ጊዜ የምንደኝነቱን ሥራ ሁለት እጥፍ አድርጎ ስድስት ዓመት አገልግሎሃልና አይክበድህ፤ አምላክህም እግዚአብሔር በምትሠራው ሁሉ ይባርክሃል።
19ላምህና በግህ የወለዱትን ተባት የሆነውን በኵራት ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ትቀድሳለህ፤ በበሬህ በኵራት አትሥራበት፥ የበግህንም በኵራት አትሸልት።
20አምላክህ እግዚአብሔር በመረጠው ስፍራ አንተና ቤተ ሰብህ በየዓመቱ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ብሉአቸው።
21ነውረኛ ወይም አንካሳ ወይም ዕውር ቢሆን፥ ወይም አንዳች ክፉ ነውር ቢኖረው፥ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አትሠዋው።
22በአገርህ ደጅ ውስጥ ትበላዋለህ፤ ንጹሕ ሰው ንጹሕም ያልሆነ ሚዳቋና ዋላ እንደሚበሉ ይበሉታል።
23ነገር ግን ደሙን እንደ ውኃ በምድር ላይ አፍስሰው እንጂ አትብላው።