English

ምዕራፍ 33

1የእግዚአብሔር ሰው ሙሴ ሳይሞት የእስራኤልን ልጆች የባረከባት በረከት ይህች ናት።
2እንዲህም አለ። እግዚአብሔር ከሲና መጣ፥ በሴይርም ተገለጠ፤ ከፋራን ተራራ አበራላቸው፥ ከአእላፋትም ቅዱሳኑ መጣ፤ በስተ ቀኙም የእሳት ሕግ ነበረላቸው።
3ሕዝቡንም ወደዳቸው፤ ቅዱሳኑ ሁሉ በእጅህ ናቸው፤ በእግሮችህም አጠገብ ተቀመጡ፤ ቃሎችህን ይቀበላሉ።
4ሙሴ ለያዕቆብ ጉባኤ ርስት የሆነውን ሕግ አዘዘን።
5የሕዝቡ አለቆች ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ ጋር በተከማቹ ጊዜ፥ ንጉሥ በይሹሩን ነበረ።
6ሮቤል በህይወት ይኑር፥ አይሙት፤ ሰዎቹም በቍጥር ብዙ ይሁኑ።
7የይሁዳ በረከት ይህ ነው፤ እንዲህም አለ። አቤቱ፥ የይሁዳን ድምፅ ስማ፥ ወደ ወገኖቹም አግባው፤ እጆቹ ይጠንክሩለት፤ በጠላቶቹ ላይ ረዳት ትሆነዋለህ።
8ስለ ሌዊም እንዲህ አለ፥ ቱሚምህና ኡሪምህ ለቅዱስህ ሰው ነው፥ በማሳህ ለፈተንኸው፥ በመሪባ ውኃም ለተከራከርኸው፤
9ስለ አባቱና ስለ እናቱ። አላየሁም ላለ፥ ወንድሞቹንም ላላስተዋለ፥ ልጆቹንም ላላወቀ፤ ቃልህን አደረጉ፥ ቃል ኪዳንህንም ጠበቁ።
10ፍርድህን ለያዕቆብ፥ ሕግህንም ለእስራኤል ያስተምራሉ፤ በፊትህ ዕጣንን፥ በመሠዊያህም የሚቃጠል መሥዋዕት ይሠዋሉ።
11አቤቱ፥ ሀብቱን ባርክ፥ የእጁንም ሥራ ተቀበል፤ የሚነሣበትን ወገብ ውጋው፥ የሚጠሉትም አይነሡ።
12ስለ ብንያምም እንዲህ አለ። በእግዚአብሔር የተወደደ በእርሱ ዘንድ ተማምኖ ይኖራል፤ ቀኑን ሁሉ ይጋርደዋል፥ በትከሻውም መካከል ያድራል።
13ስለ ዮሴፍም እንዲህ አለ፥ ምድሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተባረከ ይሁን፤ በሰማያት ገናንነት በጠል፥ በታችኛውም ቀላይ፥
14በፀሐዩ ፍሬያት ገናንነት፥ በጨረቃውም መውጣት ገናንነት
15በቀደሙትም ተራሮች ከፍተኛነት፥ በዘላለሙም ኮረብቶች ገናንነት፥
16በምድሪቱም ገናንነትና ሞላዋ፥ በቍጥቋጦው ውስጥ ከነበረው በረከት በዮሴፍ ራስ ላይ፥ ከወንድሞቹም በተለየው ራስ አናት ላይ ይውረድ።
17ለላሞች በኵር ግርማ ይሆናል፤ ቀንዶቹ አንድ ቀንድ እንዳለው ናቸው፤ በእነርሱ እስከ ምድር ዳርቻ ያሉትን አሕዛብ ሁሉ ይወጋል፤ የኤፍሬም እልፍ አእላፋት፥ የምናሴም አእላፋት እነርሱ ናቸው።
18ስለ ዛብሎንም እንዲህ አለ። ዛብሎን ሆይ፥ በመውጣትህ፥ ይሳኮር ሆይ፥ በድንኳንህ ውስጥ ደስ ይበላችሁ።
19የተሰወረውን የአሸዋውን መዝገብ፥ የባሕሩንም ባለጠግነት ይጠባሉና አሕዛብን ወደ ተራራው ይጠራሉ፤ በዚያ የጽድቅ መሥዋዕት ይሠዋሉ።
20ስለ ጋድም እንዲህ አለ። ጋድን ሰፊ ያደረገ ቡሩክ ይሁን፤ እንደ አንበሳይቱ ዐርፎአል፤ ክንድንና ራስን ይቀጠቅጣል።
21በዚያ የአለቃ እድል ፈንታ ቀርቶአልና የመጀመሪያውን ክፍል ለራሱ መረጠ፤ ወደ ሕዝብ አለቆችም መጣ፤ የእግዚአብሔርንም ጽድቅ፥ ፍርዱንም ከእስራኤል ጋር አደረገ።
22ስለ ዳንም እንዲህ አለ። ዳን የአንበሳ ደቦል ነው፤ ከባሳን ዘልሎ ይወጣል።
23ስለ ንፍታሌምም እንዲህ አለ። ንፍታሌም በሞገስ ጠግቦአል፥ የእግዚአብሔርንም በረከት ተሞልቶአል፤ ባሕሩንና ደቡቡን ይወርሳል።
24ስለ አሴርም እንዲህ አለ። አሴር በልጆች የተባረከ ይሁን፤ በወንድሞቹ የተወደደ ይሁን፤ እግሩንም በዘይት ውስጥ ያጥልቅ።
25ጫማህ ብረትና ናስ ይሆናል፤ እንደ ዕድሜህ እንዲሁ ኃይልህ ይሆናል።
26ይሹሩን ሆይ፥ በሰማያት ላይ ለረድኤትህ፥ በደመናትም ላይ በታላቅነት እንደሚሄድ እንደ እግዚአብሔር ያለ ማንም የለም።
27መኖሪያህ የዘላለም አምላክ ነው፥ የዘላለምም ክንዶች ከአንተ በታች ናቸው፤ ጠላትህን ከፊትህ አውጥቶ። አጥፋው ይላል።
28እስራኤልም ተማምኖ፥ የያዕቆብም ምንጭ ብቻውን፥ እህልና የወይን ጠጅ ባለባት ምድር ይኖራል፤ ሰማያቱም ጠልን ያንጠባጥባሉ።
29እስራኤል ሆይ፥ ምስጉን ነህ፤ በእግዚአብሔር የዳነ ሕዝብ እንደ አንተ ማን ነው? እርሱ የረድኤትህ ጋሻ፥ የከፍተኛነትህም ሰይፍ ነው። ጠላቶችህም ይገዙልሃል፤ አንተም ከፍታቸውን ትረግጣለህ።