ምዕራፍ 16
1ከኤሊምም ተጓዙ፥ የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ከግብፅ አገር ከወጡ በኋላ በሁለተኛው ወር ከወሩም በአሥራ አምስተኛው ቀን በኤሊምና በሲና መካከል ወዳለችው ወደ ሲን ምድረ በዳ መጡ።
2የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ በምድረ በዳ በሙሴና በአሮን ላይ አንጐራጐሩ።
3የእስራኤልም ልጆች። ይህን ጉባኤ ሁሉ በራብ ልትገድሉ እኛን ወደዚች ምድረ በዳ አውጥታችኋል፤ በሥጋው ምንቸት አጠገብ ተቀምጠን እንጀራ ስንበላ ስንጠግብ ሳለን በግብፅ ምድር በእግዚአብሔር እጅ ምነው በሞትን! አሉአቸው።
4እግዚአብሔርም ሙሴን። በሕጌ ይሄዱ ወይም አይሄዱ እንደሆነ እኔ እንድፈትናቸው፥ እነሆ ከሰማይ እንጀራን አዘንብላችኋለሁ፤ ሕዝቡም ወጥተው ለዕለት ለዕለት የሚበቃቸውን ይልቀሙ።
5እንዲህም ይሆናል፤ በስድስተኛው ቀን ያመጡትን ያዘጋጁ፥ ዕለት ዕለትም ከሚለቅሙት ይልቅ ሁለት እጥፍ ይሁን አለው።
6ሙሴና አሮንም ለእስራኤል ልጆች ሁሉ። እግዚአብሔር ከግብፅ ምድር እንዳወጣችሁ ማታ ታውቃላችሁ፥
7የእግዚአብሔርንም ክብር ጥዋት ታያላችሁ፤ በእግዚአብሔር ላይ ያንጐራጐራችሁትን ሰምቶአልና በእኛም ላይ የምታንጐራጕሩ እኛ ምንድር ነን? አሉ።
8ሙሴም። እግዚአብሔር ያንጐራጐራችሁበትን ማንጐራጐራችሁን ሰምቶአልና በመሸ ጊዜ ትበሉ ዘንድ ሥጋን፥ ማልዶም ትጠግቡ ዘንድ እንጀራን እግዚአብሔር ይሰጣችኋል፤ እኛም ምንድር ነን? ማንጐራጐራችሁ በእግዚአብሔር ላይ ነው እንጂ በእኛ አይደለም አለ።
9ሙሴም አሮንን። ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ። ማንጐራጐራችሁን ሰምቶአልና ወደ እግዚአብሔር ፊት ቅረቡ በል አለው።
10እንዲህም ሆነ፤ አሮን ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በተናገረ ጊዜ ወደ ምድረ በዳ ፊታቸውን አቀኑ፤ እነሆም የእግዚአብሔር ክብር በደመናው ታየ።
11
12እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። የእስራኤልን ልጆች ማንጐራጐር ሰማሁ። ወደ ማታ ሥጋን ትበላላችሁ፥ ማለዳም እንጀራን ትጠግባላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ በላቸው።
13እንዲህም ሆነ፤ በመሸ ጊዜ ድርጭቶች መጡ፥ ሰፈሩንም ከደኑት፤ ማለዳም በሰፈሩ ዙሪያ ጠል ወድቆ ነበር።
14የወደቀውም ጠል ባለፈ ጊዜ፥ እነሆ በመሬት ላይ እንደ ደቃቅ ውርጭ ሆኖ ቅርፊት የሚመስል ደቃቅ ነገር በምድረ በዳ ታየ።
15የእስራኤልም ልጆች ባዩት ጊዜ ያ ምን እንደ ሆነ አላወቁምና እርስ በእርሳቸው። ይህ ምንድር ነው? ተባባሉ። ሙሴም። ትበሉት ዘንድ እግዚአብሔር የሰጣችሁ እንጀራ ነው።
16እግዚአብሔር ያዘዘው ነገር ይህ ነው። እያንዳንዱ የሚበላውን ያህል ይልቀም፤ በድኳኑ ባሉት ነፍሶች ቍጥር ለአንድ ሰው አንድ ጎሞር ውሰዱ አላቸው።
17የእስራኤልም ልጆች እንዲሁ አደረጉ፤ አንዱ አብዝቶ አንዱም አሳንሶ ለቀመ።
18በጎሞርም በሰፈሩት ጊዜ እጅግ ለለቀመ አልተረፈውም ጥቂትም ለለቀመ አልጐደለበትም፤ ሁሉ እያንዳንዱ የሚበላውን ያህል ለቀመ።
19ሙሴም። ማንም ከእርሱ አንዳች ለነገ አያስቀር አላቸው።
20ነገር ግን ሙሴን አልሰሙትም፤ አንዳንድ ሰዎችም ከእርሱ ለነገ አስቀሩ፥ እርሱም ተላ ሸተተም፤ ሙሴም ተቈጣቸው።
21ሰውም ሁሉ ዕለት ዕለት የሚበላውን ያህል በጥዋት ለቀመ፤ ፀሐይም በተኰሰ ጊዜ ቀለጠ።
22እንዲህም ሆነ፤ በስድስተኛው ቀን ሁለት እጥፍ አድርገው እያንዳንዳቸው ሁለት ጎሞር እንጀራ ለቀሙ፤ የማኀበሩም አለቆች ሁሉ መጥተው ለሙሴ ነገሩት።
23እርሱም። እግዚአብሔር የተናገረው ይህ ነው። ነገ ዕረፍት፥ ለእግዚአብሔርም የተቀደሰ ሰንበት ነው፤ የምትጋግሩትን ጋግሩ፥ የምትቀቅሉትንም ቀቅሉ፥ የተረፈውን ሁሉ ለነገ እንዲጠበቅ አኑሩት አላቸው።
24ሙሴም እንዳዘዘ ለነገ አኖሩት፤ አልሸተተም፥ ትልም አልሆነበትም።
25ሙሴም። የእግዚአብሔር ሰንበት ዛሬ ነውና ብሉት፤ ዛሬ በሜዳ አታገኙትም።
26ስድስት ቀን ልቀሙት፤ ሰባተኛው ቀን ግን ሰንበት ነው፤ በእርሱ አይገኝም አለ።
27በሰባተኛውም ቀን እንዲህ ሆነ፤ ከሕዝቡ አንዳንድ ሰዎች ሊለቅሙ ወጡ፥ ምንምን አላገኙም።
28እግዚአብሔርም ሙሴን። ትእዛዞቼንና ሕጎቼን ለመጠበቅ እስከ መቼ እንቢ ትላላችሁ?
29እግዚአብሔር ሰንበትን እንደ ሰጣችሁ እዩ፤ ስለዚህ በስድስተኛው ቀን የሁለት ቀን እንጀራ ሰጣችሁ፤ ሰው ሁሉ በስፍራው ይቀመጥ፥ በሰባተኛው ቀን ማንም ከስፍራው አይሂድ አለው።
30ሕዝቡም በሰባተኛው ቀን ዐረፈ።
31የእስራኤልም ወገን ስሙን መና ብለው ጠሩት፤ እርሱም እንደ ድንብላል ዘር ነጭ ነው፤ ጣዕሙም እንደ ማር ቂጣ ነው።
32ሙሴም። እግዚአብሔር ያዘዘው ነገር ይህ ነው። ከግብፅ ምድር ባወጣኋችሁ ጊዜ በምድረ በዳ ያበላኋችሁን እንጀራ ያዩ ዘንድ ከእርሱ አንድ ጎሞር ሙሉ ለልጅ ልጆቻችሁ ይጠበቅ አለ።
33ሙሴም አሮንን። አንድ ማድጋ ወስደህ ጎሞር ሙሉ መና አግባበት፥ ለልጅ ልጃችሁም ይጠበቅ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት አኑረው አለው።
34እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ ይጠበቅ ዘንድ አሮን በምስክሩ ፊት አኖረው።
35የእስራኤልም ልጆች ወደሚኖሩባት ምድር እስኪመጡ ድረስ አርባ ዓመት መና በሉ፤ ወደ ከነዓን ምድር ድንበር እስኪመጡ ድረስ መና በሉ።
36ጎሞርም የኢፍ መስፈሪያ አሥረኛ ክፍል ነው።