ምዕራፍ 2
1ከሌዊ ወገንም አንድ ሰው ሄዶ የሌዊን ልጅ አገባ።
2ሴቲቱም ፀነሰች፥ ወንድ ልጅም ወለደች፤ መልካምም እንደሆነ ባየች ጊዜ ሦስት ወር ሸሸገችው።
3ደግሞም ልትሸሽገው ባልቻለች ጊዜ፥ የደንገል ሣጥን ለእርሱ ወስዳ ዝፍትና ቅጥራን ለቀለቀችው፤ ሕፃኑንም አኖረችበት፥ በወንዝም ዳር ባለ በቄጠማ ውስጥ አስቀመጠችው።
4እኅቱም የሚደረግበትን ታውቅ ዘንድ በሩቅ ቆማ ትጎበኘው ነበር።
5የፈርዖንም ልጅ ልትታጠብ ወደ ወንዝ ወረደች፤ ደንገጥሮችዋም በወንዝ ዳር ይሄዱ ነበር፤ ሣጥኑንም በቄጠማ ውስጥ አየች፥ ደንገጥርዋንም ልካ አስመጣችው።
6በከፈተችውም ጊዜ ሕፃኑን አየች፥ እነሆም ሕፃኑ ያለቅስ ነበር፤ አዘነችለትም። ይህ ከዕብራውያን ልጆች አንድ ነው አለች።
7እኅቱም ለፈርዖን ልጅ። ሕፃኑን ታጠባልሽ ዘንድ ሄጄ የምታጠባ ሴት ከዕብራውያን ሴቶች ልጥራልሽን? አለቻት።
8የፈርዖንም ልጅ። ሂጂ አለቻት፤ ብላቴናይቱም ሄዳ የሕፃኑን እናት ጠራች።
9የፈርዖንም ልጅ። ይህን ሕፃን ወስደሽ አጥቢልኝ፥ ዋጋሽንም እሰጥሻለሁ አለቻት። ሴቲቱም ሕፃኑን ወስዳ አጠባችው።
10ሕፃኑም አደገ፥ ወደ ፈርዖንም ልጅ ዘንድ አመጣችው፥ ለእርስዋም ልጅ ሆነላት። እኔ ከውኃ አውጥቼዋለሁና ስትልም ስሙን ሙሴ ብላ ጠራችው።
11በዚያም ወራት እንዲህ ሆነ፤ ሙሴ ጎበዝ በሆነ ጊዜ ወደ ወንድሞቹ ወጣ፥ የሥራቸውንም መከራ ተመለከተ፤ የግብፅም ሰው የወንድሞቹን የዕብራውያንን ሰው ሲመታ አየ።
12ወዲህና ወዲያም ተመለከተ፥ ማንንም አላየም፥ ግብፃዊውንም ገደለ፥ በአሸዋም ውስጥ ሸሸገው።
13በሁለተኛውም ቀን ወጣ፥ ሁለቱም የዕብራውያን ሰዎች ሲጣሉ አየ፤ በዳዩንም። ለምን ባልንጀራህን ትመታዋለህ? አለው።
14ያም። በእኛ ላይ አንተን አለቃ ወይስ ዳኛ ማን አደረገህ? ወይስ ግብፃዊውን እንደ ገደልኸው ልትገድለኝ ትሻለህን? አለው። ሙሴም። በእውነት ይህ ነገር ታውቆአል ብሎ ፈራ።
15ፈርዖንም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ ሙሴን ሊገድለው ፈለገ። ሙሴ ግን ከፈርዖን ፊት ኰበለለ፥ በምድያምም ምድር ተቀመጠ፤ በውኃም ጕድጓድ አጠገብ ዐረፈ።
16ለምድያምም ካህን ሰባት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም መጥተው ውኃ ቀዱ፥ የአባታቸውንም በጎች ሊያጠጡ የውኃውን ገንዳ ሞሉ።
17እረኞችም መጥተው ገፉአቸው፤ ሙሴ ግን ተነሥቶ ረዳቸው፥ በጎቻቸውንም አጠጣላቸው።
18ወደ አባታቸው ወደ ራጉኤልም በመጡ ጊዜ። ስለ ምን ዛሬ ፈጥናችሁ መጣችሁ? አላቸው።
19እነርሱም። አንድ የግብፅ ሰው ከእረኞች እጅ አዳነን፥ ደግሞም ቀዳልን፥ በጎቻችንንም አጠጣ አሉ።
20ልጆቹንም። እርሱ ወዴት ነው? ለምንስ ያንን ሰው ተዋችሁት? ጥሩት እንጀራም ይብላ አላቸው።
21ሙሴም ከዚያ ሰው ጋር ሊቀመጥ ወደደ፤ ልጁንም ሲፓራን ለሙሴ ሚስት ትሆነው ዘንድ ሰጠው።
22ወንድ ልጅም ወለደች። በሌላ ምድር መጻተኛ ነኝ ሲል ስሙን ጌርሳም ብሎ ጠራው።
23ከዚያም ከብዙ ቀን በኋላ እንዲህ ሆነ፤ የግብፅ ንጉሥ ሞተ፤ የእስራኤልም ልጆች ከባርነት የተነሣ አለቀሱ፥ ጮኹም፥ ስለ ባርነታቸውም ጩኸታቸው ወደ እግዚአብሔር ወጣ።
24እግዚአብሔርም የለቅሶአቸውን ድምፅ ሰማ፥ እግዚአብሔርም ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን አሰበ።
25እግዚአብሔርም የእስራኤልን ልጆች አየ፥ እግዚአብሔርም በእነርሱ ያለውን ነገር አወቀ።