ምዕራፍ 18
1በቀትርም ጊዜ እርሱ በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር በመምሬ የአድባር ዛፍ ተገለጠለት።
2ዓይኑንም አነሣና እነሆ፥ ሦስት ሰዎች በፊቱ ቆመው አየ፤ ባያቸውም ጊዜ ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ደጃፍ ተነሥቶ ሮጠ፥ ወደ ምድርም ሰገደ፥ እንዲህም አለ።
3አቤቱ፥ በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ ባሪያህን አትለፈኝ ብዬ እለምናለሁ፤
4ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ፥ እግራችሁን ታጠቡ፥ ከዚህችም ዛፍ በታች ዕረፉ፤
5ቍራሽ እንጀራም ላምጣላችሁ፥ ልባችሁንም ደግፋ ከዚያም በኋላ ትሄዳላችሁ፤ ስለዚህ ወደ ባሪያችሁ መጥታችኋልና። እነርሱም። እንዳልህ አድርግ አሉት።
6አብርሃምም ወደ ድንኳን ወደ ሣራ ዘንድ ፈጥኖ ገባና። ሦስት መስፈሪያ የተሰለቀ ዱቄት ፈጥነሽ አዘጋጂ፥ ለውሺውም፥ እንጎቻም አድርጊ አላት።
7አብርሃምም ወደ ላሞቹ ሮጠ፥ እጅግ የሰባም ታናሽ ጥጃ ያዘና ለብላቴናው ሰጠው፥ ያዘጋጅም ዘንድ ተቻኰለ።
8እርጎና ወተትም ያዘጋጀውንም ጥጃ አመጣ፥ በፊታቸውም አቀረበው፤ እርሱም ከዛፉ በታች በፊታቸው ቆሞ ነበር፥ እነርሱም በሉ።
9እነርሱም። ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት? አሉት። እርሱም። በድንኳኑ ውስጥ ናት አላቸው።
10እርሱም። የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለሁ፤ ሚስትህ ሣራም ልጅን ታገኛለች አለ። ሣራም በድንኳን ደጃፍ በስተ ኋላው ሳለች ይህንን ሰማች።
11አብርሃምና ሣራም በዕድሜአቸው ሸምግለው ፈጽመው አርጅተው ነበር፤ በሴቶች የሚሆነውም ልማድ ከሣራ ተቋርጦ ነበር።
12ሣራም በልብዋ እንዲህ ስትል ሳቀች። ካረጀሁ በኋላ በውኑ ፍትወት ይሆንልኛልን? ጌታዬም ፈጽሞ ሸምግሎአል።
13እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው። ካረጀሁ በኋላ በውኑ እወልዳለሁን? ስትል ሣራ ለምን ሳቀች?
14በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን? የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ እመለሳለሁ፤ ሣራም ልጅን ታገኛለች።
15ሣራም ስለ ፈራች። አልሳቅሁም ስትል ካደች። እርሱም። አይደለም፥ ሳቅሽ እንጂ አላት።
16ሰዎቹም ከዚያ ተነሥተው ወደ ሰዶም አቀኑ፤ አብርሃምም ሊሸኛቸው አብሮአቸው ሄደ።
17እግዚአብሔርም አለ። እኔ የማደርገውን ከአብርሃም እሰውራለሁን?
18አብርሃም በእውነት ታላቅና ብርቱ ሕዝብ ይሆናልና፥ የምድር አሕዛብም ሁሉ በእርሱ ይባረካሉና።
19ጽድቅንና ፍርድን በማድረግ የእግዚአብሔርን መንገድ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቹንና ከእርሱ በኋላ ቤቱን እንዲያዝዝ አውቃለሁና፤ ይህም እግዚአብሔር በአብርሃም ላይ የተናገረውን ነገር ሁሉ ያመጣ ዘንድ ነው።
20እግዚአብሔርም አለ። የሰዶምና የገሞራ ጩኸት እጅግ በዝቶአልና፥ ኃጢአታቸውም እጅግ ከብዳለችና፥
21እንግዲህስ ወደ እኔ እንደ መጣች እንደ ጩኸትዋ አድርገው እንደ ሆነ ወርጄ አያለሁ፤ እንዲሁም ባይሆን አውቃለሁ።
22ሰዎቹም ከዚያ ፊታቸውን አቀኑ፥ ወደ ሰዶምም ሄዱ፤ አብርሃም ግን በእግዚአብሔር ፊት ገና ቆሞ ነበር።
23አብርሃምም ቀረበ አለም። በውኑ ጻድቁን ከኃጢአተኛ ጋር ታጠፋለህን?
24አምሳ ጻድቃን በከተማይቱ ውስጥ ቢገኙ በውኑ ሁሉን ታጠፋለህን? ከተማይቱንስ በእርስዋ ስለሚገኙ አምሳ ጻድቃን አትምርምን?
25ይህ ከአንተ ይራቅ፤ ጻድቁን ከኃጢአተኛ ጋር ትገድል ዘንድ፥ ጻድቁም እንደ ኃጢአተኛ ይሆን ዘንድ፥ እንደዚህ ያለው አድራጎት ከአንተ ይራቅ። የምድር ሁሉ ፈራጅ በቅን ፍርድ አይፈርድምን?
26እግዚአብሔርም። በሰዶም በከተማይቱ ውስጥ አምሳ ጻድቃን ባገኝ ስፍራውን ሁሉ ስለ እነርሱ እምራለሁ አለ።
27አብርሃምም መለሰ አለም። እኔ አፈርና አመድ ስሆን ከጌታዬ ጋር እናገር ዘንድ እነሆ አንድ ጊዜ ጀመርሁ፤
28ከአምሳው ጻድቃን አምስት ቢጐድሉ ከተማይቱን ሁሉ በአምስቱ ምክንያት ታጠፋለህን? ከዚያ አርባ አምስት ባገኝ አላጠፋትም አለ።
29ደግሞም ተናገረው፥ እንዲህም አለ። ምናልባት ከዚያ አርባ ቢገኙሳ? እርሱም። ለአርባው ስል አላደርገውም አለ።
30እርሱም። ጌታዬ አይቆጣ እኔም እናገራለሁ ምናልባት ከዚያ ሠላሳ ቢገኙሳ? አለ። እርሱም ከዚያ ሰላሳ ባገኝ አላጠፋም አለ።
31ደግሞም። እነሆ፥ ከጌታዬ ጋር እናገር ዘንድ አንድ ጊዜ ጀመርሁ፤ ምናልባት ከዚያ ሀያ ቢገኙሳ? አለ። እርሱም። ከዚያ ሀያ ቢገኙ ስለ ሀያው አላደርገውም አለ።
32እርሱም። እኔ ደግሞ አንድ ጊዜ ብቻ ብናገር ጌታዬ አይቆጣ፤ ምናልባት ከዚያ አሥር ቢገኙሳ? አለ። እርሱም። ስለ አሥሩ አላጠፋትም አለ።
33እግዚአብሔርም ከአብርሃም ጋር ንግግሩን በጨረሰ ጊዜ ሄደ፤ አብርሃምም ወደ ስፍራው ተመለሰ።