English

ምዕራፍ 20

1አብርሃምም ከዚያ ተነሥቶ ወደ አዜብ ምድር ሄደ፥ በቃዴስና በሱር መካከልም ተቀመጠ፤ በጌራራም በእንግድነት ተቀመጠ።
2አብርሃምም ሚስቱን ሣራን። እኅቴ ናት አለ፤ የጌራራ ንጉሥ አቢሜሌክም ላከና ሣራን ወሰዳት።
3እግዚአብሔርም ሌሊት በሕልም ወደ አቢሜሌክ መጣ፥ እንዲህም አለው። እነሆ፥ አንተ ስለ ወሰድሃት ሴት ምውት ነህ፤ እርስዋ ባለ ባል ናትና።
4አቢሜሌክ ግን አልቀረባትም ነበር፤ እንዲህም አለ። አቤቱ፥ ጻድቁን ሕዝብ ደግሞ ታጠፋለህን?
5እኅቴ ናት ያለኝ እርሱ አይደለምን? እርስዋም ደግሞ ራስዋ። ወንድሜ ነው አለች፤ በልቤ ቅንነትና በእጄ ንጹሕነት ይህንን አደረግሁ።
6እግዚአብሔርም በሕልም አለው። ይህን በልብህ ቅንነት እንዳደረግህ እኔ አወቅሁ፥ እኔም ደግሞ በፊቴ ኃጢአትን እንዳትሠራ ከለከልሁህ፤ ስለዚህም ትነካት ዘንድ አልተውሁም።
7አሁንም የሰውዬውን ሚስት መልስ፤ ነቢይ ነውና፥ ስለ አንተም ይጸልያል፥ ትድናለህም። ባትመልሳት ግን አንተ እንድትሞት ለአንተ የሆነውም ሁሉ እንዲሞት በእርግጥ እወቅ።
8አቢሜሌክም በነገታው ማለደ፥ ባሪያዎቹንም ሁሉ ጠራ፥ ይህንንም ነገር ሁሉ በጆሮአቸው ተናገረ፤ ሰዎቹም እጅግ ፈሩ።
9አቢሜሌክም አብርሃምን ጠርቶ አለው። ይህ ያደረግህብን ምንድር ነው? ምንስ ክፉ ሠራሁብህ? በእኔና በመንግሥቴ ላይ ትልቅ ኃጢአት አውርደሃልና፤ የማይገባ ሥራ በእኔ ሠራህብኝ።
10አቢሜሌክም አብርሃምን አለው። ይህን ማድረግህ ምን አይተህ ነው?
11አብርሃምም አለ። በዚህ ስፍራ እግዚአብሔርን መፍራት በእውነት እንደሌለ፥ ለሚስቴም ሲሉ እንደሚገድሉኝ ስላሰብሁ ነው።
12እርስዋም ደግሞ በእውነት እኅቴ ናት፤ የእናቴ ልጅ አይደለችም እንጂ የአባቴ ልጅ ናት፤ ለእኔም ሚስት ሆነች።
13እግዚአብሔርም ከአባቴ ቤት ባወጣኝ ጊዜ አልኋት። በገባንበት አገር ሁሉ ለእኔ የምታደርጊው ወሮታ ይህ ነው። ወንድሜ ነው ብለሽ ስለ እኔ ተናገሪ።
14አቢሜሌክም በጎችንና ላሞችን ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎችን አመጣ፥ ለአብርሃምም ሰጠው፥ ሚስቱን ሣራንም መለሰለት።
15አቢሜሌክም። እነሆ፥ ምድሬ በፊትህ ናት፤ በወደድኸው ተቀመጥ አለ።
16ሣራንም አላት። እነሆ፥ ለወንድምሽ ሺህ ሚዛን ብር ሰጠሁት፤ ያም እነሆ ከአንቺ ጋር ባሉት ሁሉ ፊት የዓይኖች መሸፈኛ ይሁንሽ፤ ጽድቅሽ ለሰዎች ሁሉ ተገልጦአልና።
17አብርሃምም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም አቢሜሌክን ሚስቱንም ባሪያዎቹንም ፈወሳቸው፥ እነርሱም ወለዱ፤
18እግዚአብሔር በአብርሃም ሚስት በሣራ ምክንያት በአቢሜሌክ ቤት ማኅፀኖችን ሁሉ በፍጹም ዘግቶ ነበርና።