ምዕራፍ 27
1ይስሐቅ ሸምግሎ ዓይኖቹ ከማየት በፈዘዙ ጊዜ ታላቁን ልጁን ዔሳውን ጠርቶ። ልጄ ሆይ አለው፤ እርሱም። እነሆ አለሁ አለው።
2እርሱም አለው። እነሆ እኔ አረጀሁ፥ የምሞትበትን ቀን አላውቅም።
3አሁንም ማደኛህን የፍላጻህን አፎትና ቀስትህን ውሰድ፥ ወደ ምድረ በዳም ውጣ፥ አደንም አድንልኝ፤
4ሳልሞትም ነፍሴ እንድትባርክህ የጣፈጠ መብል እኔ እንደምወደው አዘጋጅተህ እበላ ዘንድ አምጣልኝ።
5ርብቃም ይስሐቅ ለልጁ ለዔሳው ሲነግር ትሰማ ነበር። ዔሳውም አደን አድኖ ሊያመጣ ወደ ምድረ በዳ ሄደ።
6ርብቃም ልጅዋን ያዕቆብን እንዲህ አለችው። እነሆ፥ አባትህ ለወንድምህ ለዔሳው።
7አደን አድነህ አምጣልኝ፥ ሳልሞትም በልቼ በእግዚአብሔር ፊት እንድባርክህ የጣፈጠ መብል አድርግልኝ ብሎ ሲነግረው ሰማሁ።
8አሁንም፥ ልጄ ሆይ፥ እኔ በማዝዝህ ነገር ስማኝ፤
9ወደ መንጋ ሄደህ ሁለት መልካካም ጠቦቶች አምጣልኝ፤ እነርሱንም ጣፋጭ መብል ለአባትህ እንደሚወደው አደርጋለሁ፤
10ለአባትህም፥ ሳይሞት እንዲባርክህ፥ ይበላ ዘንድ ታገባለታለህ።
11ያዕቆብም ርብቃን እናቱን አላት። እነሆ ዔሳው ወንድሜ ጠጕራም ሰው ነው፥ እኔ ግን ለስላሳ ነኝ፤
12ምናልባት አባቴ ቢዳስሰኝ በፊቱ እንደሚዘብት እሆናለሁ፤ መርገምንም በላዬ አመጣለሁ፥ በረከትን አይደለም።
13እናቱም አለችው። ልጄ ሆይ፥ መርገምህ በእኔ ላይ ይሁን፤ ቃሌን ብቻ ስማኝ፤ ሂድና አምጣልኝ።
14ሄዶም አመጣ፥ ለእናቱም ሰጣት፤ እናቱም የጣፈጠውን መብል አባቱ እንደሚወደው አደረገች።
15ርብቃም ከእርስዋ ዘንድ በቤት የነበረችውን የታላቁን ልጅዋን የዔሳውን መልካሙን ልብስ አመጣች፥ ታናሹን ልጅዋን ያዕቆብንም አለበሰችው፤
16የጠቦቶችንም ለምድ በእጆቹና በለስላሳው አንገቱ ላይ አደረገች፤
17የሠራችውን ጣፋጭ መብልና እንጀራውን ለልጅዋ ለያዕቆብ በእጁ ሰጠችው።
18ወደ አባቱም ገብቶ። አባቴ ሆይ አለው እርሱም። እነሆኝ፤ ልጄ ሆይ፥ አንተ ማን ነህ? አለ።
19ያዕቆብም አባቱን አለው። የበኵር ልጅህ እኔ ዔሳው ነኝ፤ እንዳዘዝኽኝ አደረግሁ፤ ነፍስህ ትባርከኝ ዘንድ ቀና በልና ተቀመጥ፥ ካደንሁትም ብላ።
20ይስሐቅም ልጁን። ልጄ ሆይ፥ እንዴት ፈጥነህ አገኘኸው? አለው። እርሱም። እግዚአብሔር አምላክህ ወደ እኔ ስለ አቀረበው ነው አለ።
21ይስሐቅም ያዕቆብን። ልጄ ሆይ፥ አንተ ልጄ ዔሳው እንደ ሆንህ ወይም እንዳልሆንህ እዳስስህ ዘንድ ቅረበኝ አለው።
22ያዕቆብም ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ቀረበ፤ ዳሰሰውም፥ እንዲህም። ይህ ድምፅ የያዕቆብም ድምፅ ነው፥ እጆች ግን የዔሳው እጆች ናቸው አለው።
23እርሱም አላወቀውም ነበር፤ እጆቹ እንደ ወንድሙ እንደ ዔሳው እጆች ጠጕራም ነበሩና፤ ስለዚህም ባረከው።
24አለውም። አንተ ልጄ ዔሳው ነህን? እርሱም። እኔ ነኝ አለ።
25እርሱም። ከልጄ አደን እንድበላና ነፍሴ እንድትባርክህ አቅርብልኝ አለ። አቀረበለትም፥ በላም፤ የወይን ጠጅ አመጣለት፥ እርሱም ጠጣ።
26አባቱ ይስሐቅም። ልጄ ሆይ፥ ወደ እኔ ቅረብ ሳመኝም አለው።
27ወደ እርሱም ቀረበ፥ ሳመውም፤ የልብሱንም ሽታ አሸተተ፥ ባረከውም፥ እንዲህም አለ። የልጄ ሽታ እግዚአብሔር እንደ ባረከው እርሻ ሽታ ነው፤
28እግዚአብሔርም ከሰማይ ጠል ከምድርም ስብ የእህልንም የወይንንም ብዛት ይስጥህ፤
29አሕዛብ ይገዙልህ ሕዝብም ይስገዱልህ፤ ለወንድሞችህ ጌታ ሁን፥ የእናትህም ልጆች ይስገዱልህ፤ የሚረግምህ እርሱ ርጉም ይሁን የሚባርክህም ቡሩክ ይሁን።
30ይስሐቅም ያዕቆብን ባርኮ ከፈጸመ በኋላ፥ ያዕቆብም ከአባቱ ከይስሐቅ ፊት ከወጣ በኋላ፥ ወዲያው በዚያው ጊዜ ዔሳው ከአደኑ መጥቶ ገባ።
31እርሱም ደግሞ ጣፋጭ መብል አዘጋጀ፥ ለአባቱም አገባ፤ አባቱንም። አባቴ ይነሣ፥ ነፍስህም ትባርከኝ ዘንድ ከልጁ አደን ይብላ አለው።
32አባቱ ይስሐቅም። አንተ ማን ነህ? አለው፤ እርሱም። እኔ የበኵር ልጅህ ዔሳው ነኝ አለው።
33ይስሐቅም እጅግ ደነገጠ እንዲህም አለ። ያደነውን አደን ወደ እኔ ያመጣ ማን ነው? አንተ ሳትመጣም ከሁሉ በላሁ ባረክሁትም፤ እርሱም የተባረከ ሆኖ ይኖራል።
34ዔሳውም የአባቱን ቃል በሰማ ጊዜ ታላቅ እጅግም መራራ ጩኸት ጮኸ፥ አባቱንም። አባቴ ሆይ፥ እኔንም ደግሞ ባርከኝ አለው።
35እርሱም። ወንድምህ በተንኮል ገብቶ በረከትህን ወሰደብህ አለ።
36እርሱም አለ። በእውነት ስሙ ያዕቆብ ተባለ፥ ሁለት ጊዜ አሰናክሎኛልና፤ ብኵርናዬን ወሰደ፥ አሁንም እነሆ በረከቴን ወሰደ። ደግሞም። ለእኔ በረከትን አላስቀረህልኝምን? አለ።
37ይስሐቅም መለሰ ዔሳውንም አለው። እነሆ፥ ጌታህ አደረግሁት፥ ወንድሞቹንም ሁሉ ለእርሱ ተገዦች ይሆኑ ዘንድ ሰጠሁት፥ በእህልም በወይንም አበረታሁት፤ ለአንተ ግን፥ ልጄ ሆይ፥ ምን ላድርግ?
38ዔሳውም አባቱን አለው። አባቴ ሆይ፥ በረከትህ አንዲት ብቻ ናትን? አባቴ ሆይ፥ እኔንም ደግሞ ባርከኝ። ዔሳውም ቃሉን አንሥቶ አለቀሰ።
39አባቱ ይስሐቅም መለሰ አለውም። እነሆ፥ መኖሪያህ ከምድር ስብ ከላይ ከሚገኝ ከሰማይም ጠል ይሆናል፤
40በሰይፍህም ትኖራለህ፥ ለወንድምህም ትገዛለህ፤ ነገር ግን በተቃወምኸው ጊዜ ቀንበሩን ከአንገትህ ትጥላለህ።
41ዔሳውም አባቱ ስለ ባረከው በያዕቆብ ቂም ያዘበት፤ ዔሳውም በልቡ አለ። ለአባቴ የልቅሶ ቀን ቀርቦአል፥ ከዚያም በኋላ ወንድሜን ያዕቆብን እገድለዋለሁ።
42ለርብቃም ይህ የታላቁ ልጅዋ የዔሳው ቃል ደረሰላት፤ ታናሹን ልጅዋን ያዕቆብንም አስጠርታ አስመጣችው፥ አለችውም። እነሆ፥ ወንድምህ ዔሳው ሊገድልህ ይፈቅዳል።
43አሁንም ልጄ ሆይ ቃሌን ስማ፤ ተነሣና ወደ ካራን ምድር ወደ ወንድሜ ወደ ላባ ሂድ፤
44በእርሱም ዘንድ ጥቂት ቀን ተቀመጥ፥ የወንድምህ ቍጣ እስኪበርድ ድረስ፤
45የወንድምህ ቍጣ ከአንተ እስኪመለስ ድረስ፥ ያደረግህበትንም እስኪረሳው ድረስ፤ ከዚያም ልኬ አስመጣሃለሁ፤ በአንድ ቀን ሁለታችሁን ለምን አጣለሁ?
46ርብቃም ይስሐቅን አለችው። ከኬጢ ሴቶች ልጆች የተነሣ ሕይወቴን ጠላሁት፤ ያዕቆብ ከዚህ አገር ሴቶች ልጆች ሚስትን የሚያገባ ከሆነ በሕይወት መኖር ለምኔ ነው?