English

ምዕራፍ 34

1ለያዕቆብ የወለደችለት የልያ ልጅ ዲናም የዚያን አገር ሴቶች ልጆችን ለማየት ወጣች።
2የአገሩ አለቃ የኤዊያዊ ሰው የኤሞር ልጅ ሴኬም አያት፤ ወሰዳትም ከእርስዋም ጋር ተኛ፥ አስነወራትም።
3ልቡናውም በያዕቆብ ልጅ በዲና ፍቅር ተነደፈ፥ ብላቴናይቱንም ወደዳት፥ ልብዋንም ደስ በሚያሰኛት ነገር ተናገራት።
4ሴኬምም አባቱን ኤሞርን። ይህችን ብላቴና አጋባኝ ብሎ ነገረው።
5ያዕቆብም ልጁን ዲናን እንዳስነወራት ሰማ፤ ልጆቹም ከከብቶቻቸው ጋር በምድረ በዳ ነበሩ፤ ያዕቆብም እስኪመጡ ድረስ ዝም አለ።
6የሴኬም አባት ኤሞርም ይነግረው ዘንድ ወደ ያዕቆብ ወጣ።
7የያዕቆብም ልጆች ይህንን በሰሙ ጊዜ ከምድረ በዳ መጡ፤ የያዕቆብን ልጅ በመተኛቱ በእስራኤል ላይ ስንፍናን ስላደረገ አዘኑ፥ እጅግም ተቈጡ፤ እንዲህ አይደረግምና።
8ኤሞርም እንዲህ ብሎ ነገራቸው። ልጄ ሴኬም በልጃችሁ ፍቅር ልቡ ተነድፎአልና ሚስት እንድትሆነው እባካችሁ እርስዋን ስጡት።
9ጋብቾችም ሁኑን፤ ሴቶች ልጆቻችሁን ስጡን፥ እናንተም የእኛን ሴቶች ልጆች ውሰዱ።
10ከእኛም ጋር ተቀመጡ፥ ምድሪቱም በፊታችሁ ናት፤ ኑሩባት፥ ነግዱም፥ ግዙአትም።
11ሴኬምም አባትዋንና ወንድሞችዋን እንዲህ አለ። በፊታችሁ ሞገስን ባገኝ የምትሉኝን እሰጣለሁ።
12ብዙ ማጫና እጅ መንሻ አምጣ በሉኝ፥ በነገራችሁኝም መጠን እሰጣለሁ፤ ይህችን ብላቴና ግን አጋቡኝ።
13የያዕቆብም ልጆች ለሴኬምና ለአባቱ ለኤሞር በተንኰል መለሱ፥ እኅታቸውን ዲናን አርክሶአታልና፤
14እንዲህም አሉአቸው። እኅታችንን ላልተገረዘ ሰው ለመስጠት ይህንን ነገር እናደርግ ዘንድ አይቻለንም፤ ይህ ነውር ይሆንብናልና።
15እንደ እኛ ሆናችሁ ወንዶቻችሁን ሁሉ ብትገርዙ በዚህ ብቻ እሺ እንላችኋለን፤
16ሴቶች ልጆቻችንን እንሰጣችኋለን፥ የእናንተንም ሴቶች ልጆች እንወስዳለን፤ አንድ ሕዝብም ሆነን ከእናንተ ጋር እንኖራለን።
17ትገረዙ ዘንድ እኛን ባትሰሙ ግን ልጃችንን ይዘን እንሄዳለን።
18ነገራቸውም በኤሞር ልጅ በሴኬምና በኤሞር ዘንድ የተወደደ ሆነ።
19ብላቴናውም ያሉትን ያደርግ ዘንድ አልዘገየም፥ የያዕቆብን ልጅ ወድዶአልና፤ እርሱም በአባቱ ቤት ካሉት ሁሉ የከበረ ነበረ።
20ኤሞርና ሴኬም ልጁም ወደ ከተማቸው አደባባይ ገቡ፥ ለከተማቸውም ሰዎች እንዲህ ብለው ነገሩ።
21እነዚህ ሰዎች በእኛ ዘንድ የሰላም ሰዎች ናቸው፤ በምድራችን ይቀመጡ፥ ይነግዱባትም፥ እነሆም ምድሪቱ ሰፊ ናት፤ ሴቶች ልጆቻቸውን እንውሰድ፥ ለእነርሱም ሴቶች ልጆቻችንን እንስጥ።
22ነገር ግን አንድ ሕዝብ ሆነን ከእኛ ጋር ይቀመጡ ዘንድ በዚህ ነገር ብቻ እሺ ይሉናል፤ እነርሱ እንደ ተገረዙ ወንዶቻችንን ሁሉ ብንገርዝ።
23ከብቶቻቸውም ያላቸውም ሁሉ እንስሶቻቸውም ሁሉ ለእኛ አይደሉምን? በዚህ ነገር ብቻ እሺ ያልናቸው እንደ ሆነ ከእኛ ጋር ይቀመጣሉ።
24ከከተማይቱም አደባባይ የሚወጡ ሁሉ ኤሞርንና ልጁን ሴኬምን እሺ አሉ፤ ከከተማይቱ አደባባይ የሚወጡት ወንዶች ሁሉ ተገረዙ።
25ሦስተኛም ቀን በሆነ ጊዜ እጅግ ቆስለው ሳሉ፥ የዲና ወንድሞች የያዕቆብ ልጆች ስምዖንና ሌዊ እየራሳቸው ሰይፋቸውን ይዘው ሳይፈሩ ወደ ከተማ ገቡ፥ ወንዱንም ሁሉ ገደሉ፤
26ኤሞርንና ልጁን ሴኬምንም በሰይፍ ገደሉ፥ እኅታቸውን ዲናንም ከሴኬም ቤት ይዘው ወጡ።
27የያዕቆብም ልጆች እኅታቸውን ዲናን ሰለ አረከሱአት ወደ ሞቱት ገብተው ከተማይቱን ዘረፉ፤
28በጎቻቸውንም ላሞቻቸውንም አህዮቻቸውንም በውጭም በከተማም ያለውን ወሰዱ።
29ሀብታቸውን ሁሉ ሕፃናቶቻቸውንና ሴቶቻቸውንም ሁሉ ማረኩ፥ በቤት ያለውንም ሁሉ ዘረፉ።
30ያዕቆብም ሌዊንና ስሞዖንን እንዲህ አለ። በዚች አገር በሚኖሩ በከነዓናውያንና በፌርዛውያን ሰዎች የተጠላሁ ታደርጉኝ ዘንድ እኔን አስጨነቃችሁኝ፤ እኔ በቍጥር ጥቂት ነኝ፤ እነርሱ በእኔ ላይ ይሰበሰቡና ይመቱኛል፤ እኔም ከወገኔ ጋር እጠፋለሁ።
31እነርሱም። በጋለሞታ እንደሚደረግ በእኅታችን ያደርግባትን? አሉ። a