English

ምዕራፍ 36

1የዔሳው ትውልድ ይህ ነው፤ እርሱም ኤዶም ነው።
2ዔሳው ከከነዓን ልጆች ሚስቶችን አገባ፤ የኬጢያዊውን የዔሎንን ልጅ ዓዳን፥ የኤዊያዊው የፅብዖን ልጅ ዓና የወለዳትን አህሊባማን፥
3የእስማኤልን ልጅ የነባዮትን እኅት ቤሴሞትን።
4ዓዳ ለዔሳው ኤልፋዝን ወለደች፤ ቤሴሞትም ራጉኤልን ወለደች፤
5አህሊባማም የዑስን፥ የዕላምን፥ ቆሬን ወለደች፤ በከነዓን ምድር የተወለዱለት የዔሳው ልጆች እነዚህ ናቸው።
6ዔሳውም ሚስቶቹን ወንዶች ልጆቹንና ሴቶች ልጆቹን ቤተሰቡንም ሁሉ ከብቱንም ሁሉ እንስሶቹንም ሁሉ በከነዓንም አገር ያገኘውን ሁሉ ይዞ ከወንድሙ ከያዕቆብ ፊት ወደ ሌላ አገር ሄደ።
7ከብታቸው ስለ በዛ በአንድነት ይቀመጡ ዘንድ አልቻሉም፤ በእንግድነት የተቀመጡባትም ምድር ከከብታቸው ብዛት የተነሣ ልትበቃቸው አልቻለችም።
8ዔሳውም በሴይር ተራራ ተቀመጠ፤ ዔሳውም ኤዶም ነው።
9በሴይር ተራራ የሚኖሩ የኤዶማውያን አባት የዔሳው ትውልድም ይህ ነው።
10የዔሳው ልጆች ስም ይህ ነው፤ የዔሳው ሚስት የዓዳ ልጅ ኤልፋዝ፤ የዔሳው ሚስት የቤሴሞት ልጅ ራጉኤል።
11የኤልፋዝም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ቴማን፥ ኦማር፥ ስፎ፥ ጎቶም፥ ቄኔዝ።
12ቲምናዕም ለዔሳው ልጅ ለኤልፋዝ የጭን ገረድ ነበረች፥ አማሌቅንም ለኤልፋዝ ወለደችለት፤ የዔሳው ሚስት የዓዳ ልጆች እነዚህ ናቸው።
13የራጉኤልም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ናሖት፥ ዛራ፥ ሣማ፥ ሚዛህ፤ እነዚህም የዔሳው ሚስት የቤሴሞት ልጆች ናቸው።
14የፅብዖን ልጅ የዓና ልጅ የዔሳው ሚስት የአህሊባማ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ለዔሳውም የዑስን፥ የዕላማን፥ ቆሬን ወለደች።
15የዔሳው ልጆች አለቆች እነዚህ ናቸው፤ ለዔሳው የበኵር ለኤልፋዝ ልጆች፤ ቴማን አለቃ፥ ኦማር አለቃ፥ ስፎ አለቃ፥ ቄኔዝ አለቃ፥
16ቆሬ አለቃ፥ ጎቶም አለቃ፥ አማሌቅ አለቃ፤ በኤዶም ምድር የኤልፋዝ አለቆች እነዚህ ናቸው፤ እነዚህ የዓዳ ልጆች ናቸው።
17የዔሳው ልጅ የራጉኤል ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ናሖት አለቃ፥ ዛራ አለቃ፥ ሣማ አለቃ፥ ሚዛህ አለቃ፤ በኤዶም ምድር የራጉኤል ልጆች አለቆች እነዚህ ናቸው፤ እነዚህም የዔሳው ሚስት የቤሴሞት ልጆች ናቸው።
18የዔሳው ሚስት የአህሊባማ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ የዑስ አለቃ፥ የዕላማ አለቃ፥ ቆሬ አለቃ፤ የዔሳው ሚስት የዓና ልጅ የአህሊባማ አለቆች እነዚህ ናቸው።
19የዔሳው ልጆችና አለቆቻቸው እነዚህ ናቸው፤ እርሱም ኤዶም ነው።
20በዚያች አገር የተቀመጡ የሖሪው የሴይር ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ሎጣን፥ ሦባል፥ ፅብዖን፥ ዓና፥ ዲሶን፥ ኤጽር፥ ዲሳን፤
21እነዚህ በኤዶም ምድር የሖሪው የሴይር ልጆች አለቆች ናቸው።
22የሎጣን ልጆችም ሖሪ፥ ሄማም ናቸው፤ የሎጣንም እኅት ቲምናዕ ናት።
23የሦባል ልጆችም እነዚህ ናቸው፤ ዓልዋን፥ ማኔሐት፥ ዔባል፥ ስፎ፥ አውናም።
24የፅብዖን ልጆችም እነዚህ ናቸው፤ አያ፥ ዓና፤ ይህም ዓና በምድረ በዳ የአባቱን የፅብዖንን አህዮች ሲጠብቅ ፍልውኆችን ያገኘ ነው።
25የዓና ልጆችም እነዚህ ናቸው፤
26ዲሶን፥ አህሊባማም የዓና ሴት ልጅ። የዲሶንም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ሔምዳን፥ ኤስባን፥ ይትራን፥ ክራን።
27የኤጽር ልጆችም እነዚህ ናቸው፤ ቢልሐን፥ ዛዕዋን፥ ዓቃን።
28የዲሳን ልጆችም እነዚህ ናቸው፤ ዑፅ፥ አራን።
29የሖሪ አለቆች እነዚህ ናቸው፤ ሎጣን አለቃ፥ ሦባል አለቃ፥ ፅብዖን አለቃ፥
30ዓና አለቃ፥ ዲሶን አለቃ፥ ኤጽር አለቃ፥ ዲሳን አለቃ፤ በሴይር ምድር አለቆች የሆኑ የሖሪ አለቆቹ እነዚህ ናቸው።
31በእስራኤል ልጆች ላይ ንጉሥ ከመኖሩ በፊት በኤዶም አገር የነገሡ ነገሥታት እነዚህ ናቸው።
32በኤዶምም የቢዖር ልጅ ባላቅ ነገሠ፤ የከተማውም ስም ዲንሃባ ናት።
33ባላቅም ሞተ፥ በስፍራውም የባሶራው የዛራ ልጅ ኢዮባብ ነገሠ።
34ኢዮባብም ሞተ፥ በስፍራውም የቴማኒው አገር ሑሳም ነገሠ።
35ሑሳምም ሞተ፥ በስፍራውም የምድያምን ሰዎች በሞዓብ ሜዳ የመታ የባዳድ ልጅ ሃዳድ ነገሠ፤ የከተማውም ስም ዓዊት ተባለ።
36ሃዳድም ሞተ፥ በስፍራውም የመሥሬቃው ሠምላ ነገሠ።
37ሠምላም ሞተ፥ በስፍራውም በወንዝ አጠገብ ካለችው ከርሆቦት ሳኦል ነገሠ።
38ሳኦልም ሞተ፥ በስፍራውም የዓክቦር ልጅ በኣልሐናን ነገሠ።
39የዓክቦር ልጅ በኣልሐናንም ሞተ፥ በስፍራውም ሃዳር ነገሠ፤ የከተማውም ስም ፋዑ ነው፤ ሚስቱም የሜዛሃብ ልጅ መጥሬድ የወለደቻት መሄጣብኤል ትባላለች።
40የዔሳውም የአለቆቹ ስም በወገናቸው በስፍራቸው በስማቸውም ይህ ነው፤ ቲምናዕ አለቃ፥ ዓልዋ አለቃ፥ የቴት አለቃ፥
41አህሊባማ አለቃ፥ ኤላ አለቃ፥ ፊኖን አለቃ፥
42ቄኔዝ አለቃ፥ ቴማን አለቃ፥ ሚብሳር አለቃ፥
43መግዲኤል አለቃ፥ ዒራም አለቃ፥ እነዚህ በግዛታቸው ምድር በየመኖሪያቸው የኤዶም አለቆች ናቸው። የኤዶማውያን አባት ይህ ዔሳው ነው። a