ምዕራፍ 4
1አዳምም ሚስቱን ሔዋንን አወቀ፤ ፀነሰችም፥ ቃየንንም ወለደች። እርስዋም። ወንድ ልጅ ከእግዚአብሔር አገኘሁ አለች።
2ደግሞም ወንድሙን አቤልን ወለደች። አቤልም በግ ጠባቂ ነበረ፤ ቃየንም ምድርን የሚያርስ ነበረ።
3ከብዙ ቀን በኋላም ቃየን ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን አቀረበ፤
4አቤልም ደግሞ ከበጎቹ በኵራትና ከስቡ አቀረበ። እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፤
5ወደ ቃየንና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም። ቃየንም እጅግ ተናደደ ፊቱም ጠቆረ።
6እግዚአብሔርም ቃየንን አለው። ለምን ተናደድህ? ለምንስ ፊትህ ጠቆረ?
7መልካም ብታደርግ ፊትህ የሚበራ አይደለምን? መልካም ባታደርግ ግን ኃጢአት በደጅ ታደባለች፤ ፈቃድዋም ወደ አንተ ነው፥ አንተ ግን በእርስዋ ንገሥባት።
8ቃየንም ወንድሙን አቤልን። ና ወደ ሜዳ እንሂድ አለው። በሜዳም ሳሉ ቃየን በወንድሙ በአቤል ላይ ተነሣበት፥ ገደለውም።
9እግዚአብሔርም ቃየንን አለው። ወንድምህ አቤል ወዴት ነው? እርሱም አለ። አላውቅም፤ የወንድሜ ጠባቂው እኔ ነኝን?
10አለውም። ምን አደረግህ? የወንድምህ የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል።
11አሁንም የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፍዋን በከፈተች በምድር ላይ አንተ የተረገምህ ነህ።
12ምድርንም ባረስህ ጊዜ እንግዲህ ኃይልዋን አትሰጥህም፤ በምድርም ላይ ኰብላይና ተቅበዝባዥ ትሆናለህ።
13ቃየንም እግዚአብሔርን አለው። ኃጢአቴ ልሸከማት የማልችላት ታላቅ ናት።
14እነሆ ዛሬ ከምድር ፊት አሳደድኸኝ፤ ከፊትህም እሰወራለሁ፤ በምድርም ላይ ኰብላይና ተቅበዝባዥ እሆናለሁ፤ የሚያገኘኝም ሁሉ ይገድለኛል።
15እግዚአብሔርም እርሱን አለው። እንግዲህ ቃየንን የገደለ ሁሉ ሰባት እጥፍ ይበቀልበታል። እግዚአብሔርም ቃየንን ያገኘው ሁሉ እንዳይገድለው ምልክት አደረገለት።
16ቃየንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ፤ ከዔድንም ወደ ምሥራቅ በኖድ ምድር ተቀመጠ።
17ቃየንም ሚስቱን አወቀ፤ ፀነሰችም፥ ሄኖሕንም ወለደች። ከተማም ሠራ፥ የከተማይቱንም ስም በልጁ ስም ሄኖሕ አላት።
18ሄኖሕም ጋይዳድን ወለደ፤ ጋይዳድም ሜኤልን ወለደ፤ ሜኤልም ማቱሣኤልን ወለደ፤ ማቱሣኤልም ላሜሕን ወለደ።
19ላሜሕም ለራሱ ሁለት ሚስቶችን አገባ፤ የአንዲቱ ስም ዓዳ፥ የሁለተኛይቱ ስም ሴላ ነበረ።
20ዓዳም ያባልን ወለደች፤ እርሱም በድንኳን የሚቀመጡት የዘላኖች አባት ነበረ።
21የወንድሙም ስም ዩባል ነበረ፤ እርሱም በገናንና መለከትን ለሚይዙ አባት ነበረ።
22ሴላም ደግሞ ከናስና ከብረት የሚቀጠቀጥ ዕቃን የሚሠራውን ቱባልቃይንን ወለደች። የቱባልቃይንም እኅት ናዕማ ነበረች።
23ላሜሕም ለሚስቶቹ ለዓዳና ለሴላ አላቸው። እናንት የላሜሕ ሚስቶች ቃሌን ስሙ፥ ነገሬንም አድምጡ፤ እኔ ጕልማሳውን ለቍስሌ፥ ብላቴናውንም ለመወጋቴ ገድዬዋለሁና፤
24ቃየንን ሰባት እጥፍ ይበቀሉታል፤ ላሜሕን ግን ሰባ ሰባት እጥፍ። ይበቀሉታል
25አዳም ደግሞ ሚስቱን አወቀ፤ ወንድ ልጅንም ወለደች። ስሙንም። ቃየን በገደለው በአቤል ፋንታ እግዚአብሔር ሌላ ዘር ተክቶልኛል ስትል ሴት አለችው።
26ለሴት ደግሞ ወንድ ልጅ ተወለደለት፤ ስሙንም ሄኖስ አለው፤ በዚያን ጊዜም በእግዚአብሔር ስም መጠራት ተጀመረ።