ምዕራፍ 40
1ከዚህ ነገር በኋላም እንዲህ ሆነ፤ የግብፅ ንጉሥ የጠጅ አሳላፊና የእንጀራ አበዛ ጌታቸውን የግብፅ ንጉሥን በደሉ።
2ፈርዖንም በሁለቱ ሹማምቱ በጠጅ አሳላፊዎቹ አለቃና በእንጀራ አበዛዎቹ አለቃ ላይ ተቆጣ፤
3ዮሴፍ ታስሮ በነበረበትም በግዞት ስፍራ በዘበኞቹ አለቃ ቤት አስጠበቃቸው።
4የዘበኞቹም አለቃ ለዮሴፍ አሳልፎ ሰጣቸው፥ እርሱም ያገለግላቸው ነበር፤ በግዞት ቤትም አያሌ ቀን ተቀመጡ።
5በግዞት ቤት የነበሩት የግብፅ ንጉሥ ጠጅ አሳላፊና እንጀራ አበዛ ሁለቱም በአንዲት ሌሊት እንደ ሕልሙ ትርጓሜ እየራሳቸው ሕልምን አለሙ።
6ዮሴፍም ማልዶ ወደ እነርሱ ገባ፥ እነሆም አዝነው አያቸው።
7በጌታው ቤት ከእርሱ ጋር በግዞት የነበሩትንም የፈርዖንን ሹማምት እንዲህ ብሎ ጠየቃቸው። እናንተ ዛሬ ስለ ምን አዝናችኋል?
8እነርሱም። ሕልምን አልመን የሚተረጕምልን አጣን አሉት። ዮሴፍም አላቸው። ሕልምን የሚተረጕም እግዚአብሔር የሰጠው አይደለምን? እስቲ ንገሩኝ።
9የጠጅ አሳላፊዎች አለቃም ለዮሴፍ ሕልሙን እንዲህ ብሎ ነገረው። በሕልሜ የወይን ዛፍ በፊቴ ሆና አየሁ፥
10በዛፊቱም ሦስት አረግ አለባት፤ እርስዋም ቅጠልና አበባ አወጣች፥ ዘለላም አንጠለጠለች፥ የዘለላዋም ፍሬ በሰለ፤
11የፈርዖንም ጽዋ በእጄ ነበረ፤ ፍሬውንም ወስጄ በፈርዖን ጽዋ ጨመቅሁት፥ ጽዋውንም ለፈርዖን በእጁ ሰጠሁት።
12ዮሴፍም አለው። የዚህ ትርጓሜው ይህ ነው፤ ሦስቱ አረግ ሦስት ቀን ነው፤
13እስከ ሦስት ቀን ድረስ ፈርዖን ራስህን ከፍ ያደርጋል፥ ወደ ቀደመው ሹመትህም ይመልስሃል፤ ጠጅ አሳላፊ በነበርህበት ጊዜ ስታደርግ እንደ ነበረው እንደ ቀድሞው ሥርዓትም የፈርዖንን ጽዋ በእጁ ትሰጣለህ።
14ነገር ግን በጎ ነገር በተደረገልህ ጊዜ እኔን አስበኝ፥ ምሕረትንም አድርግልኝ፥ የእኔንም ነገር ለፈርዖን ነግረህ ከዚህ ቤት አውጣኝ፤
15እኔን ከዕብራውያን አገር ሰርቀው አምጥተውኛልና፤ ከዚህም ደግሞ በግዞት ያኖሩኝ ዘንድ ምንም አላደረግሁም።
16የእንጀራ አበዛዎቹ አለቃም ሕልሙን በመልካም እንደ ተረጎመ ባየ ጊዜ ዮሴፍን እንዲህ አለው። እኔም ደግሞ ሕልም አይቼ ነበር፥ እነሆም ሦስት መሶብ ነጭ እንጀራ በራሴ ላይ ነበረ፤
17በላይኛውም መሶብ ፈርዖን ከሚበላው ከጋጋሪዎች ሥራ ሁሉ ነበረበት፤ ወፎችም በራሴ ላይ ከመሶቡ ይበሉ ነበር።
18ዮሴፍም መልሶ እንዲህ አለው። የዚህ ትርጓሜው ይህ ነው፤ ሦስቱ መሶብ ሦስት ቀን ነው፤
19እስከ ሦስት ቀን ድረስ ፈርዖን ራስህን ከፍ ያደርጋል፥ በእንጨትም ላይ ይሰቅልሃል፤ ወፎችም ሥጋህን ይበሉታል።
20በሦስተኛውም ቀን ፈርዖን የተወለደበት ቀን ነበረ፥ ለሠራዊቱም ሁሉ ግብር አደረገ፤ የጠጅ አሳላፊዎቹን አለቃና የእንጀራ አበዛዎቹን አለቃ በአሽከሮቹ መካከል ከፍ አደረገ።
21የጠጅ አሳለፊዎቹንም አለቃ ወደ ስፍራው መለሰው፥ ጽዋውንም በፈርዖን እጅ ሰጠ፤
22የእንጀራ አበዛዎቹንም አለቃ ሰቀለው፥ ዮሴፍ እንደተረጎመላቸው።
23የጠጅ አሳላፊዎች አለቃ ግን ዮሴፍን አላሰበውም፥ ረሳው እንጂ።