ምዕራፍ 42
1ያዕቆብም በግብፅ እህል እንዳለ ሰማ፥ ያዕቆብም ልጆቹን። ለምን እርስ በርሳችሁ ትተያያላችሁ? አላቸው።
2እንዲህም አለ። እነሆ ስንዴ በግብፅ እንዲገኝ ሰምቼአለሁ፤ ወደዚያ ውረዱ፥ እንድንድንና እንዳንሞትም ከዚያ ሸምቱልን።
3የዮሴፍም አሥሩ ወንድሞቹ ስንዴን ከግብፅ ይሸምቱ ዘንድ ወረዱ፤
4የዮሴፍን ወንድም ብንያምን ግን ያዕቆብ ከወንድሞቹ ጋር አልሰደደውም። ምናልባት ክፉ እንዳያገኘው ብሎአልና።
5የእስራኤልም ልጆች ለእህል ሸመታ ከመጡቱ ጋር ገቡ፤ በከነዓን አገር ራብ ነበረና።
6ዮሴፍም በምድር ላይ ገዥ ነበረ፥ እርሱም ለምድር ሕዝብ ሁሉ ይሸጥ ነበር፤ የዮሴፍም ወንድሞች በመጡ ጊዜ በምድር ላይ በግምባራቸው ሰገዱለት።
7ዮሴፍም ወንድሞቹን አይቶ አወቃቸው፤ ተለወጠባቸውም፥ ክፉ ቃልንም ተናገራቸው። እናንተ ከወዴት መጣችሁ? አላቸው። እነርሱም። ከከነዓን ምድር እህል ልንሸምት የመጣን ነን አሉት።
8ዮሴፍም ወንድሞቹን አወቃቸው፥ እነርሱ ግን አላወቁትም፤
9ዮሴፍም ስለ እነርሱ አይቶት የነበረውን ሕልም አሰበ። እንዲህም አላቸው። እናንተ ሰላዮች ናችሁ፤ የምድሩን ዕራቁትነት ልታዩ መጥታችኋል።
10እነርሱም አሉት። ጌታችን ሆይ አይደለም፤ ባሪያዎችህ ስንዴን ሊገዙ መጥተዋል፤
11እኛ ሁላችን የአንድ ሰው ልጆች ነን፤ እኛ እውነተኞች ነን፥ ባሪያዎችህስ ሰላዩች አይደሉም።
12እርሱም አላቸው። አይደለም፤ ነገር ግን የአገሩን ዕራቁትነት ልታዩ መጥታችኋል።
13እነርሱም አሉ። ባሪያዎችህ አሥራ ሁለት ወንድማማች በከነዓን ምድር የአንድ ሰው ልጆች ነን፤ ታናሹም እነሆ ዛሬ ከአባታችን ጋር ነው፥ አንዱም ጠፍቶአል።
14ዮሴፍም አላቸው። እናንተ ሰላዮች ናችሁ ብዬ የተናገርኋችሁ ይህ ነው፤
15በዚህ ትፈተናላችሁ፤ ታናሽ ወንድማችሁ ካልመጣ በቀር የፈርዖንን ሕይወት ከዚህ አትወጡም።
16እውነትን የምትናገሩ ከሆነ ነገራችሁ ይፈተን ዘንድ ከእናንተ አንዱን ስደዱ፥ ወንድማችሁንም ይዞ ይምጣ እናንተም ታሥራችሁ ተቀመጡ፤ ይህ ካልሆነ የፈርዖንን ሕይወት ሰላዮች ናችሁ።
17ሦስት ቀን ያህል በግዞት ቤት ጨመራቸው።
18በሦስተኛውም ቀን ዮሴፍ እንዲህ አላቸው። ትድኑ ዘንድ ይህን አድርጉ፤ እኔ እግዚአብሔርን እፈራለሁና።
19እናንተ የታመናችሁ ከሆናችሁ ከእናንተ አንዱ ወንድማችሁ በግዞታችሁ ቤት ይታሰር እናንተ ግን ሂዱ፥ እህሉንም ለቤታችሁ ራብ ውሰዱ፤
20ታናሹንም ወንድማችሁን ወደ እኔ ይዛችሁ ኑ፤ ነገራችሁም የታመነ ይሆናልና አትሞቱም። እንዲህም አደረጉ።
21እነርሱም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ። በእውነት ወንድማችንን በድለናል፥ እኛን በማማጠን ነፍሱ ስትጨነቅ አይተን አልሰማነውምና፤ ስለዚህ ይህ መከራ መጣብን።
22ሮቤልም መልሶ እንዲህ አላቸው። ብላቴናውን አትበድሉ ብያችሁ አልነበረምን? እኔም አልሰማችሁኝም፤ ስለዚህ እነሆ አሁን ደሙ ይፈላለገናል።
23እነርሱም ዮሴፍ ነገራቸውን እንደሚሰማባቸው አላወቁም፥ በመካከላቸው አስተርጓሚ ነበረና።
24ከእነርሱም ዘወር ብሎ አለቀሰ፤ ደግሞም ወደ እነርሱ ተመልሶ ተናገራቸው፥ ስምዖንንም ከእነርሱ ለይቶ ወሰዶ በፊታቸው አሰረው።
25ዮሴፍም ዓይበታቸውን እህል ይሞሉት ዘንድ አዘዘ፤ የእየራሳቸውንም ብር በእየዓይበታቸው ይመልሱት ዘንድ ደግሞም የመንገድ ስንቅ ይሰጡአቸው ዘንድ አዘዘ። እንዲሁም ተደረገላቸው።
26እነርሱም እህሉን በአህዮቻቸው ላይ ጫኑ፥ ከዚያም ተነሥተው ሄዱ።
27ከእነርሱም አንዱ ባደሩበት ስፍራ ለአህያው ገፈራን ይሰጥ ዘንድ ዓይበቱን ሲፈታ ብሩን አየ፥ እነሆም በዓይበቱ አፍ ላይ ነበረች።
28ለወንድሞቹም። ብሬ ተመለሰችልኝ፥ እርስዋም በዓይበቴ አፍ እነኋት አላቸው። ልባቸውም ደነገጠ፥ እየተንቀጠቀጡም እርስ በርሳቸው ተባባሉ። እግዚአብሔር ያደረገብን ይህ ምንድር ነው?
29ወደ አባታቸውም ወደ ያዕቆብ ወደ ከነዓን ምድር መጡ፥ የደረሰባቸውንም ነገር ሁሉ እንዲህ ብለው አወሩ።
30የአገሩ ጌታ የሆነው ሰው በክፉ ንግግር ተናገረን፥ የምድሪቱም ሰላዮች አስመሰለን።
31እኛም እንዲህ አልነው። እውነተኞች ሰዎች ነን እንጂ ሰላዮች አይደለንም፤
32እኛ የአባታችን ልጆች አሥራ ሁለት ወንድማማች ነን፤ አንዱ ጠፍቶአል፥ ታናሹም በከነዓን ምድር ዛሬ ከአባታችን ጋር አለ።
33የአገሩም ጌታ ያ ሰው እንዲህ አለን። የታመናችሁ ሰዎች ከሆናችሁ በዚህ አውቃለሁ፤ አንደኛውን ወንድማችሁን ከእኔ ጋር ተዉት፥ ለቤታችሁም ራብ እህልን ወስዳችሁ ሂዱ፤
34ታናሹንም ወንድማችሁን አምጡልኝ፥ እውነተኞች እንጂ ሰላዮች አለመሆናችሁንም በዚህ አውቀዋለሁ፤ ወንድማችሁንም እሰጣችኋለሁ፥ እናንተም በምድሩ ትነግዳላችሁ።
35እንዲህም ሆነ፤ ዓይበታቸውን በፈቱ ጊዜ እነሆ ከእነርሱ እያንዳንዳቸው ብራቸውን በእየዓይበታቸው ተቋጥሮ አገኙት፤ እነርሱም አባታቸውም የብራቸውን ቍጥራት አይተው ፈሩ።
36አባታቸው ያዕቆብም እንዲህ አላቸው። ልጅ አልባ አስቀራችሁኝ፤ ዮሴፍ የለም፥ ስምዖንም የለም፥ ብንያምንም ትወስዱብኛላችሁ፤ ይህ ሁሉ በእኔ ላይ ደረሰ።
37ሮቤልም አባቱን አለው። ወደ አንተ መልሼ ያላመጣሁት እንደ ሆነ ሁለቱን ልጆቼን ግደል፤ እርሱን በእጄ ስጠኝ፥ እኔም ወደ አንተ እመልሰዋለሁ።
38እርሱም አለ። ልጄ ከእናንተ ጋር አይወርድም፤ ወንድሙ ሞቶ እርሱ ብቻ ቀርቶአልና፤ በምትሄዱበት መንገድ ምናልባት ክፉ ነገር ቢያገኘው ሽምግልናዬን በኅዘን ወደ መቃብር ታወርዱታላችሁ። a